“የሰሜን ጎንደር ነዋሪዎች በድርቁ ምክንያት ወደ ከተሞች እየተሰደዱ ነው”- ዩኤንኦቻ

የኢትዮጵያ ካርታ

Your browser doesn’t support HTML5

“የሰሜን ጎንደር ነዋሪዎች በድርቁ ምክንያት ወደ ከተሞች እየተሰደዱ ነው”- ዩኤንኦቻ

በአማራ ክልል፣ ሰሜን ጎንደር ዞን፣ ጃናሞራና ጠለምት ወረዳዎች በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከአራት ሺ በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ከቀያቸውን ለቀው ወደ ከተሞች መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (UN-OCHA) ትናንት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።

በሁለቱ ወረዳዎች በተከሰተው ድርቅ ከ86 ሺ በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸውን እና ከ173 ሺህ በላይ መሰደዳቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።

የጃን አሞራ ወረዳ ግብርና ፅ/ ቤት በበኩሉ፣ በሶስት ወራት ውስጥ ብቻ 1ሺ 4 መቶ ሰዎች ቤታቸውን ለቀው ወደ ከተሞች መሰደዳቸውን ዛሬ ለአሜሪካ ድምፅ አረጋግጠዋል።

SEE ALSO: በረሃብ የሞቱ አሉ ወይስ የሉም? ቃኝዎችና መንግሥት

ድርቁ ባስከተለው ረኀብ ምክንያት ጠለምት ወረዳን ለቀው አራት ቀን በእግር ተጉዘው በአጎራባቹ አድርቃይ ከተማ እንደሚገኙ የአሜሪካ ድምጽ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበርያ ቢሮ(UN-OCHA)፣ ከአንድ ወር በፊት ባወጣው ሪፖርቱ፣ በአማራ ክልል፣ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ ዋስትና ችግር እንዳለበት ጠቅሶ፣ የመንግሥት ምላሽ ያገኙት 25 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆኑና በስምንት ዞኖች ውስጥ የሚገኙ 713 ሺህ ሰዎች ለአደጋ እንደተጋለጡ ማመልከቱ የሚታወስ ነው፡፡

በዐማራ ክልል፣ ሰሜን ጎንደር ዞን፣ ሦስት ወረዳዎች፣ ማለትም በጃን አሞራ፣ በየዳ እና ጠለምት ወረዳዎች፣ በ2015/16 መኸር ምርት የተከሠተው ድርቅ ባስከተለው ረኀብ፣ 36 ሰዎች መሞታቸውን እና ከ72 ሺ በላይ እንስሳትም መሞታቸውን በአካባቢው የሚገኘው የደባርቅ ዩኒቨርስቲ “ከአንድ ወር በፊት አደረግኩት” ባለው ጥናት ይፋ አድርጎ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (UN-OCHA) ትናንት ባወጣው ሪፖርቱ ከድርቁ ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል፣ ጠለምትና ጃን አሞራን ጨምሮ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህፃናት ትምህርት ማቋረጣቸውንም ገልፆል።

SEE ALSO: በትግራይ ረሃብ የፌደራሉና የክልሉ እሰጥ አገባ

የፌደራል አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን እና በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ በሀገሪቱ ያለውን ወቅታዊ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በተመለከተ በጋራ ባወጡት መግለጫ በኢትዮጵያ በአምስት ክልሎች 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡