የአውሮፓ ሕብረት በአፍሪቃ ድህነትን ለመቀነስና የስደተኞችን ፍሰት ለመገደብ ሁለት ቢልዮን ዶላር እርዳታ መደበ

የአውሮፓ ሕብረት ሀገሮችና ያአፍሪቃ መሪዎች በስደተኞች ቀውስ መፍትሄ ለማግኘት ተሰብስበዋል

የአውሮፓ ሕብረትና የአፍሪቃ ሀገሮች መሪዎች ከአፍሪቃ ወደ አውሮፓ የሚጎርፉትን ስደተኞች ቁጥር ለመገደብ መፍትሄ ፍለጋ በማልታ ያደረጉትን ስብሰባ አጠናቀዋል። የአውሮፓ ሕብረት ድህነትን ለማቃለልና የስደተኞችን ፍሰት ለመገደብ የ $2 ቢልዮን ዶላር ገንዘብ መድቧል።

አፍሪቃ ወደ አውሮፓ የሚጎርፉትን ስደተኞች ለመገደብ እንድትችል ለም አቀፍ የልማት እርዳታ ያስፈልጋታል ሲሉ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦላንድ አሳስበዋል።

ፍራንሷ ኦላንድ ከ 60 በላይ የሚሆኑ የአፍሪቃና የአውሮፓ ሕብረት መሪዎች በተገኙበት ስብሰባ ላይ ሲናገሩ የአውሮፓ ህብረት ረድኤት ካላቀረበ በስተቀር በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪቃውያን ወደ አውሮፓ እንዲጎርፉ ያደረገው ቀውስ መቀጠሉ አይቀርም ብለዋል።

Your browser doesn’t support HTML5

የአውሮፓ ሕብረት በአፍሪቃ ድህነትን ለመቀነስና የስደተኞችን ፍሰት ለመገደብ ሁለት ቢልዮን ዶላር እርዳታ መደበ

ኢትዮጵያ ስደተኞች የሚወጡባትና የሚሸጋገሩባት እንዲሁም በስደተኞች መዳረሻነት ቁልፍ ሀገር በመሆናዋ ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት በፍልሰተና እንቅስቃሴ ረገድ ዛሬ በማልታው ስብሰባ የጋራ ስምምነት እንደፈረሙ የአውሮፓ ኮሚሽን ባወጠው መገለጫ ተግልጿል።

ኢትዮጵያና የአውሮፓ ሕብረት ለስደተኞች የሚያስፈልገውን ነገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ማቅረብን በሚመለከት ህጋዊና ሀገ-ወጥ ፍልሰትንና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ለመተባበር ተስማምተዋል።

ፍራንሷ ኦላንድ አብዛኞቹ አፍሪቃውያን ፈላሾች ከኤርትራና ከሱዳን የወጡ ናቸው ብለዋል።

“ከኤርትራና ከሱዳን በብዛት እየተሰደዱ ናቸው። ይህን ችግር መፍታት አለብን። በተለይም ኤርትራን አስመልክቶ ከባድ ችግር ስላለ ከፍተኛ ግፊት ማሳደር አለብን። ስለዚህ ጉዳይ ማንም እየተናገረ አይደለም። ህዝባቸው እንዲሰደድ በሚያደርጉት ሃፍረተ-ቢስ መሪዎች ምክንየት ኤርትራ ህዝብ አለባ እየሆነች ነው። አይከታተልዋቸውም። በሀገሪቱ የፖለቲካ ለውጥ መኖር አለበት። ጠንካራና ምላሽ የሚጠይቅ ዲፕሎማሲ እንዲኖር ያስፈልጋል። እኛም ይህን እያደረግን ነው። የሊብያ ጉዳይም መፍትሄ እንዲግኝለት እያሰብን ነው። በርግጥ ጊዜ መውስዱ አይቀርም። የብሄራዊ አንድነት መንግስት እንዲመሰረት፣ መነጋገር ከጀመርን ብዙ ጊዜ አልፏል። ይሁንና በተግባር ላይ ሊውል አልቻለም” ብለዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤርትራ አምባሳደር ግርማ አስመሮም በበኩላቸው የፈረንሳዩ ፕረዚዳንት አባባል ከሀቅ የራቀ ነው ብለዋል።

ከኤርትራና ከሱዳን በብዛት እየተሰደዱ ናቸው። ህዝባቸው እንዲሰደድ በሚያደርጉት ሃፍረተ-ቢስ መሪዎች ምክንየት ኤርትራ ህዝብ አለባ እየሆነች ነው።
የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦላንድ በስደተኞች

ወደ አውሮፓ ከሚጎርፉት ስድተኞች ብዛት ኤርትራውያን ከሶርያውን ቀጥሉ ከአለም የሁለተኛነት ቦታ ይዟል። ከእድሜ በታች የሆኑ ልጆች ሳይቀሩ እየተሰደዱ መሆናቸው በቴሌቪዥኖች እየታየ ነው። ሀገሪቱ ወጣት ሃይሏን እያጣች ነውና ለምንድነው መፍትሄ የማይፈለገው ለሚለው ጥያቄም አምባሳደር ግርማ አስመሮም ሀሰት ቢደጋገም እውነት ይሆናል ከሚለው አነጋገር ተነስተው ነው ይህን የሚሉትና መታረም አለብት ሲሉ መልሰዋል።

ፍራንሷ ሆላንድ ኤርትራ ህዝቧ እንዳይሰደድ ለማድረግ ሁኔታዎችን እንድታሻሻል ከፍተኛ ግፊት እንዲደረግባት ያሉትን አስመልክቶ ደግሞ አምባሳደር ግርማ ሀያላን ሀገሮች የአፍሪቃ

ቀንድንና ቀይ ባህርን ለመቆጣጠር ስለሚፈልጉ የኤርትራ መንግስት ደግሞ እንደ እንቅፋት አድርገው ስለሚቆጥሩት በኤርትራ ላይ ያላደረጉት ነገር የለም ብለዋል።

የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ሊመንበር ድላሚና ዙማ በበኩላቸው ስደተኞቹ ከየትም ይሂዱ መጥጊያ ማግኘት ይጋባቸዋል ብለዋል።

“ሰደተኞች፣ ፈላሾችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ከየትም ይሂዱ ከየት ጥገኝነት እንዲያገኙ ያስፈልጋል። የአፍሪቃ ህብረት ስደተኞችንና በሀገራቸው ውስጥ ከመኖርያቸው የተፈናቀሉት ሰዎችን እንዲሁም የህገ-ወጥ የሰዎች ሽግግር ሰለባ የሆኑትን ሁሉ ለመንከባከብ ክልላዊ ትብብር እንደሚያስፈልግ ከተገዘበ ውሎ አድሯል። ይሁንና የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን በአፍሪቃ የስደተኞች መቀበያና ማጣርያ ማዕከሎች መቋቋምን አይደግፍም። ሊቀበውም አይችልም። ስማቸው የመቀበያ ማዕከሎቹ ቢባልም እስር ቤቶች መሆናቸው አይቀርም። ይህም የስደተኞችን መብት መርገጥና መልሶ ሰለባ ማድረግ ይሆናል” ብለዋል።

በያዝነው አመት (ካለፈው ጥር ወር አንስቶ ማለት ነው) 800,000 የሚሆኑ ስደተኞች ባህርን

ተሻግረው አውሮፓ እንደገቡና ይህ አሃዝ አምና ከገቡት ወደ አራት እጥፍ እንደሚጠጋ፣ አለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት አስታውቋል። ከኤርትራ፣ ከናይጀርያ፣ ከሱዳንና ከሶማልያ የፈለሱት ሰዎች በአብዛኛው ኢጣልያ ገብተዋል። ከ 3,400 በላይ የሚሆኑ ስደተኞች በአደገኛው የጉዞ ሂደት፣ ባህር ውስጥ ሰምጠው ቀርተዋል።

የአውሮፓ ሕብረት መሪዎች ግንብ መገንባቱ የፍልሰትን ችግር አይፈታም በማለት ሲከራከሩ ቢቆዩም የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገር የሆነችው ስሎቬንያ የሰደተኞቹን ፍልሰት ለመከላከል የኤልክትሪክ ሽቦ አጥር መግንባት ጀምራለች።

የአፍሪቃ ሀገሮች በበኩላቸው የስደተኞቹን ፍሰት እንዲገድቡ ይጠበቅባቸዋል። ይሁንና እቅዱ ይሰራ እንደሆ ብዙዎች ይጠራጠራሉ። ሙሉውን ዝርዝር አዳነች ፍሰሀ አጠናቅራዋለች ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያዳምጡ።

Your browser doesn’t support HTML5

የአውሮፓ ሕብረት በአፍሪቃ ድህነትን ለመቀነስና የስደተኞችን ፍሰት ለመገደብ ሁለት ቢልዮን ዶላር እርዳታ መደበ