የጎፋ ዞን የጎርፍ ተጠቂዎች ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ድጋፍ ጠየቁ

Your browser doesn’t support HTML5

የጎፋ ዞን የጎርፍ ተጠቂዎች ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ድጋፍ ጠየቁ

በደቡብ ክልል ጎፋ ዞን ኡባ ደብረ ፀሐይ ወረዳ በደረሰው የጎርፍ አደጋ የተፈናቀሉ ሰዎች፣ ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ድጋፍ ጠየቁ። የጎፋ ዞን አስተዳደር የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም፣ ከ158 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።

SEE ALSO: በዋግኽምራ ዞን በረኀብ ተጨማሪ ዜጎች እንደሞቱና ሊከፋም እንደሚችል ተጠቆመ

የኡባ ደብረ ፀሐይ ወረዳ አስተዳዳሪ በበኩላቸው፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም፣ ከክልሉ ቀይ መስቀል እና ከአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጋራ በመተባበር፥ ቁሳቁሶች እየተሰባሰቡ፣ በጎርፍ የተጥለቀለቀው እየተጠረገ፣ የጎርፍ መውረጃው እየተጠለፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የአሜሪካ ድምፅ በስልክ ያነጋገራቸውና ጎርፍ ያፈናቀላቸው አቶ አብርሃም ዘኬዎስ፤ ቤታቸው በጎርፍ ተጠራርጎ በመወሰዱ መጠለያ አልባ መኾናቸውን ይናገራሉ። ቤታቸው ተሠርቶ ወደ ቀዬአቸው መመለሱን አብዝተው የሚፈልጉት ነገር እንደኾነ አመልክተዋል።

የስምንት ልጆች እናት መኾናቸውን የተናገሩት ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ዙፋን ታደሰም፣ ከአቶ አብርሃም ዘኬዎስ ጋራ ተመሳሳይ ጥያቄ አላቸው፡፡

የኡባ ደብረ ፀሐይ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኢልቶ ኢፀና፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም፣ ከክልሉ ቀይ መስቀል እና ከአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጋራ በመተባበር ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

ቤት ለመሥራት የሚረዱ ቁሳቁሶችን የመሰብሰብ፣ በጎርፍ የተጥለቀለቀውን የመጥረግ፣ የጎርፍ መውረጃውን የመጥለፍ ሥራ መጀመሩን፣ አቶ ኢልቶ ጨምረው ተናግረዋል።

የዞኑ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ማርቆስ መሰለ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም፣ 158 ሚሊዮን 669ሺሕ 609 ብር እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

SEE ALSO: ጎርፍ በልዩ ልዩ ክልሎች ነዋሪዎችን እያፈናቀለ ነው

አቶ ማርቆስ፣ 124 ሚሊዮን 226ሺሕ 244 የግለሰቦች ሀብት፤ ከ34 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ መሠረተ ልማቶች እና ማኅበራዊ ተቋማት መውደማቸውን አስታውቀዋል።

እንደ አቶ አብርሃም ያሉ ጎርፍ ያፈናቀላቸው ነዋሪዎች፥ ተጠልልው በሚገኙባቸው ትምህርት ቤቶች፣ ቤተ ክርስቲያንና ጤና ጣቢያ የሚደረግላቸውን ሰብአዊ ድጋፍ አድንቀው፤ በዚኽ መልኩ ግን መቀጠል ስለማይቻል፣ ለዘላቂ መፍትሔ ትኩረት እንዲሰጥ አበክረው ጠይቀዋል።

በአደጋው ለተጎዱት ነዋሪዎች፥ ከጋሞ፣ ከኮንሶ፣ ከደቡብ ኦሞ፣ ከማሌ ወረዳ እና ሌሎች አጎራባች ዞኖች እና ከክልል ቢሮዎች፣ እንዲሁም ከደቡብ ክልል ቀይ መስቀል ማኅበር፣ ሰብአዊ ድጋፍ እየቀረበላቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በኡባ ደብረ ፀሐይ ወረዳ የጎርፍ አደጋ፥ 21 ሰዎች ሲሞቱ፣ 17 ሰዎች ከባድ፣ 89 ሰዎች ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት እንደረሰባቸው ያስታወሱት አቶ ማርቆስ፣ ወረዳው በውል በአደረገው ማጣራት፣ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ5ሺሕ ወደ 2ሺሕ167 መቀነሱን አስታውቀዋል። በዚኹ ማጣራት፣ 217 ቤቶች በጎርፉ የተወሰዱ ሲኾን፣ ከ3ሺሕ500 በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸው ተረጋግጧል።