በደቡብ ክልል ጎፋ ዞን በኡባ ደብረ ፀሐይ ወረዳ የጣለው ከባድ ዝናም በአስከተለው የጎርፍ አደጋ፣ አምስት ሕፃናትን ጨምሮ 16 ሰዎች መሞታቸውን፣ የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
በአካባቢው እየጣለ ያለው ዝናም ወቅቱን የተከተለ ቢኾንም፣ በየቦታው ከተጠበቀው በላይ ከባድ ዝናም እየዘነመ በመኾኑ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ እንዳለ፣ የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገልጿል።
የደቡብ ክልል ጎፋ ዞን ኡባ ደብረ ፀሐይ ወረዳን ያጥለቀለቀው ጎርፍ ከፍተኛ መኾኑን፣ የዞኑ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሓላፊ አቶ ካሳሁን ዓባይነህ፣ በስልክ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል።
በተጨማሪም በጎርፍ አደጋው፣ ግምቱ ያልታወቀ ንብረት መውደሙንና ቁጥራቸው የበዛ የቤት እንስሳት መወሰዳቸውን አቶ ካሳሁን ተናግረዋል።
በጎርፉ ከተወሰዱ በኋላ ያልተገኙ ሰዎች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ካሳሁን፣ ፍለጋው መቀጠሉን ተናግረው፣ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ፣ ወቅቱን የጠበቀ ዝናም በተለያየ መጠን እየጣለ መኾኑን፣ በኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የትንበያ እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አሳምነው አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የክፍላተ ዘመን ቀመር መሠረት፣ ከአራቱ የዓመቱ ወቅቶች፣ በልግ ዋናው የዝናም ወቅታቸው የኾኑ አካባቢዎች፣ ከፍ ያለ የዝናም መጠን እያገኙ መኾኑን፣ ዶክተር አሳምነው ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት እየጣለ በሚገኘው ከባድ ዝናም፣ በተለያዩ አካባቢዎች ጉዳት እየደረሰ መኾኑን የጠቀሱት ሥራ አስፈጻሚው፣ ኅብረተሰቡ ማድረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ ዝርዝር ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
ጫን ባለው ዝናም ጉዳት እያስተናገዱ ያሉት ደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍሎች፣ ላለፉት አራት እና አምስት ዓመታት በራቃቸው የዝናም እርጥበት ሳቢያ፣ ድርቅ ያጋጠማቸውና ረኀብ የተከሠተባቸው አካባቢዎች እንደኾኑ መዘገቡ ይታወሳል፡፡