በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጎርፍ በልዩ ልዩ ክልሎች ነዋሪዎችን እያፈናቀለ ነው


ጎርፍ በልዩ ልዩ ክልሎች ነዋሪዎችን እያፈናቀለ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:47 0:00

ጎርፍ በልዩ ልዩ ክልሎች ነዋሪዎችን እያፈናቀለ ነው

የበልግ ዝናም ያስከተለው ጎርፍ እና የወንዞች ሙላት፣ በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ክልሎች የሚገኙ ነዋሪዎችን ማፈናቀሉን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ(OCHA) አስታወቀ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ(OCHA)፣ ትላንት በአወጣው ሪፖርቱ፣ የበልግ ዝናም ያስከተለው ጎርፍ እና የወንዞች ሙላት፥ በሶማሌ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና በአፋር ክልሎች፣ ነዋሪዎችን እያፈናቀለ መኾኑን ገልጿል።

በሶማሌ ክልል፣ ጎርፍ፣ 45 ሰዎችን መግደሉን የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ ከ35 ሺሕ በላይ አባዎራዎች መፈናቀላቸውን፣ ከ23ሺሕ በላይ እንስሳት መሞታቸውንና 99ሺሕ ሄክታር የእርሻ ማሳ መውደሙን ጠቅሷል።

የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት በበኩሉ፣ በክልሉ ውስጥ የጣለው የበልግ ዝናም በአስከተለው ጎርፍ፣ የ44 ሰዎች ሕይወት ማለፉን አስታውቋል፡፡

የክልሉ አደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ቢሮ የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቢሮ ባለፈው ሳምንት እንደገለጸው፣ በጎርፍ አደጋው፥ ከ19ሺሕ በላይ እንስሳት ሞተዋል፤ በሺሕዎች የተቆጠሩ ነዋሪዎችም ተፈናቅለዋል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል 38፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ስምንት ሰዎች፣ ለኅልፈት መዳረጋቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ሪፖርቱ አክሎም፣ በአፋር ክልል፣ 19 ሺሕ ሰዎች በጎርፉ ቀጥተኛ ተጎጂዎች መኾናቸውን፤ ዘጠኝ ሺሕ መፈናቀላቸውን፣ ከኦሮሚያ ክልልም እንዲሁ 5 ሺሕ 800 እና ከሲዳማ ከ2ሺሕ500 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ጠቅሷል።

በተጨማሪም በአጠቃላይ በተጠቀሱት ክልሎች ውስጥ በሚገኙ፤ 58 ወረዳዎች ካለፈው ነሀሴ ጀምሮ የተከሰተው የኮሌራ ወረርሺኝ 94 ሰዎችን ለሞትና 6157 ሰዎችን ለህመም መዳረጋቸውን ሪፖርቱ አስፍሯል። ለተፈናቃዮቹም ተገቢው እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው ተጠቅሷል።

በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የረጂም ጊዜ ትንበያ እና ድርቅ ክትትል ዴስክ ሓላፊ አቶ ሙሉዓለም አበራ፣ በተጠቀሱት አካባቢዎች ያለው የበልግ ዝናም እየቀነሰ እንደሚሔድ አመልክተዋል። ኾኖም፥ ሸበሌ፣ ገናሌ፣ ዳዋ፣ አዋሽ እና ኦሞ ወይም ጊቤ ወንዞች፣ መገኛቸው የክረምት ዝናም ተጠቃሚ አካባቢዎች በመኾናቸው፣ የወንዞች ሙላቱ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችል ስጋታቸውን ጠቁመዋል።

ተፈናቃዮችን ለመደገፍ፣ ባለፈው ሚያዝያ ወር፣ 170 ሺሕ ተፈናቃዮችን ለመርዳት የሚያስችል፣ የ86 ሚሊዮን ዶላር ርዳታ ተጠይቆ እንደነበር፣ የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበርያ ቢሮው አስታውሷል። ይኹንና፣ ከአወጣው ሪፖርት ዝግጅት በኋላ፣ በሸበሌ ዞን የጎርፍ መጥለቅለቅ የደረሰው ጉዳት እና የተጎጂዎች ቁጥር ማሻቀብ፣ የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን እንዳናረው ጠቁሟል።

XS
SM
MD
LG