WASHINGTON, DC —
ባለፈዉ ሳምንት ከኢትዮጵያ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር ባደረግነዉ ቃለ ምልልስ ካነሳናቸዉ ነጥቦች መካከል የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ጉዳይ አንዱ እንደነበር ይታወሳል። ዘጠኙ በአንድ መዝገብ ተከሰዉ አምስቱ ሲፈቱ አራቱ ለምን ታስረዉ እንዲቆዩ እንደተወሰነ ለዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ያቀረብነዉ ጥያቄና የሰጡት መልስ፣ የተከሳሾቹ ጠባቃ አቶ አመሃ መኮንን መልስ ለመስጠት እንዲደዉሉልን ምክንያት ሆኖአል።
ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የአምስቱ ጋዜጠኞች መፈታት ከፕሬዚደንት ኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝት ጋር ግንኙነት እንዳለዉ ተጠይቀዉ ማስተባባላቸዉ ይታወሳል።
ለአንድ ዓመት ያህል ታስረዉ የተፈቱት ጋዜጠኞች ተስፋዓለም ወልደየስ፣ ኤዶም ካሳዬ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ ዘላለም ክብረትና አስማማዉ ሃይለጊዮርጊስ ሲሆኑ አቤል ዋበላ፣ በፍቃዱ ሃይሉ፣ ናትናኤል ፈለቀና አጥናፉ ዓለማዬሁ አሁንም በእስር ቤት እንደሚገኙ ይታወቃል።
አስረኛዋ ጦማሪ ሶሊያና ሽመልስ በሌለችበት እንደተከሰሰች አይዘነጋም። አቶ አመሃ ከመንግስት በኩል ሰለታሳሪዎቹ የሚሰጠዉ መልስ የተሳሳተ ነዉ ይላሉ።
ትዝታ በላቸዉ አነጋግራቸዋለች