በዚምባብዌ፣ በሳምንቱ መጨረሻ የተካሔደውን የማሟያ ምርጫ ውጤት እንደማይቀበሉና ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ትላንት እሑድ አስታውቀዋል።
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ ዘጠኝ የማሟያ ምርጫዎች ለማድረግ ቢታቀድም፣ ውጥንቅጥ በበዛበት የቅድመ ምርጫ ሒደት፣ አብዛኛዎቹ የተቃዋሚ ዕጩዎች እንዳይወዳደሩ በፍርድ ቤት በመታገዳቸው ሳይሳተፉ ቀርተዋል።
የፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ዛኑ-ፒኢኤፍ ፓርቲ፣ ሁለት ሦስተኛውን የፓርላማ ወንበር ለመያዝና ሕገ መንግሥቱን መቀየር የሚያስችል ድምፅ ለማግኘት፣ 10 ተጨማሪ መቀመጫዎችን ማግኘት ብቻ እንደሚጠበቅበት ተነግሯል።
“ምርጫው የሐሰት ነው። ሕገ መንግሥቱንም የሚፃረር ነው፤” ሲል፣ “የዜጎች ቅንጅት ለለውጥ” የተሰኘው ዋናው ተቃዋሚ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ቅሬታውን ለሕግ ኮሚሽኑ እንደሚያሳውቅም ፓርቲው ገልጿል።
ባለፈው ነሐሴ በተደረገው ምርጫ፣ የፕሬዚዳንት ምናንጋግዋ ፓርቲ፣ ከ280 የፓርላማ መቀመጫዎች ውስጥ 177ቱን ሲያሸንፍ፣ ተቃዋሚው 104 አግኝቶ ነበር። ከሁለት ወራት በኋላ፣ 14 የፓርላማ አባላት መባረራቸውን ተከትሎ፣ ዘጠኝ የማሟያ ምርጫዎች እንዲደረጉ ተወስኖ ነበር። ቀሪዎቹ አምስት ወንበሮች፣ በተመጣጠነ ውክልና መሠረት የሚሞሉ ናቸው፤ ተብሏል።
ታዛቢዎች እንደሚሉት፣ ገዢው ዛኑ-ፒኤፍ፥ የፕሬዚዳንቱን ሁለት የሥልጣን ዘመን ገደብ በመሻር፣ የምናንጋግዋን ሥልጣን ለማስረዘም በመሞከር ላይ ነው።
መድረክ / ፎረም