በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሙጋቤን ዘልፈሻል የተባለች አሜሪካዊት ነፃ ወጣች


ማርታ ኦ’ዶኖቫን
ማርታ ኦ’ዶኖቫን

የቀድሞውን የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ሮቤርት ሙጋቤን ባለፈው ዓመት ዘልፈሻል በሚል ታስራ የነበረችን የዩናይትድ ስቴትስ ዜጋ ክሥ አንድ የሃገሪቱ ፍርድ ቤት ውድቅ አድርጎ በነፃ አሰናብቷታል።

ማርታ ኦ’ዶኖቫን ያኔ የ93 ዓመቱን ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤን የሚያዋርድና ሥልጣናቸውን የሚጋፋ ዘለፋ አድርሰሽባቸዋል ብለው ነበር ባለሥልጣናቱ ባለፈው ኅዳር መጀመሪያ ላይ የያዟት።

«ስግብግብ እና ንክ!» ብላ ነበር ትዊት ያደረገችው ኦ’ዶኖቫን። ቀደም ሲልም በፕሬዚደንቱ ላይ እንዲሁ ኃይለ-ቃላት ሠንዝራ እንደነበር ተገልጿል።

አቃቢያነ ሕጉ ክሣቸውን አጠናቅቀው ዶሴያቸውን የሚያቀርቡበትን ጊዜ ሲጠየቁ ቀን መቁረጥ ባለመቻላቸው የሃራሬው ወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛ ራምቢድዛዪ ሙጓጓ ጉዳዩን ውድቅ አደረጉት።

“ከፈለጋችኋት ካለችበት ጥሯት፤ ከእንግዲህ ይዛችሁ ልታቆይዋት አትችሉም” አሉ ዳኛው።

የሃያ አምስት ዓመቷ የማጋምባ ቴሌቪዥን ባልደረባ ማርታ ፈፅመሻል የተባለቻቸውን ፕሬዚዳንቱን የማዋረድና ሥልጣናቸውን የመጋፋት ውንጀላዎች “አልፈፀምኩም” ስትል አስተባብላለች።

ማርታ በአንድ ሺህ ዶላር ዋስ ከመለቀቋ በፊት በዚምባብዌ እጅግ የተጠናከረ ጥበቃ በሚደረግበት እሥር ቤት ውስጥ ለአንድ ሣምንት ታስራ ቆይታለች።

ለማርታ ሊከራከሩ የቆሙት የዚምባብዌ የሰብዓዊ መብቶች ጠበቆች ማኅበር አባል ኦቤይ ሻቫ ከፍርድ ቤቱ ሲወጡ ለሪፖርተሮች በሰጡት ቃል “ቀድሞም ቢሆን ጉዳይ አልነበረም - ብለዋል - መንግሥቱ ‘ጉዳይ’ ብሎት የነበረው ነገር ዛሬ ፈረሰ። እናም ፍርድ ቤቱ ቃሉን በመጠበቁ፣ ደንበኛችንንም ከተጠያቂነት ነፃ በማድረጉ በጣም ተደስተናል።”

ኦ’ዶኖቫን ባለፈው ወር ለችሎቱ አቤት ብላ በነበረ ጊዜ አቃቤ ሕግ ክሥ የሚመሠርትበትን ጊዜ ካላሳወቀ ጉዳዩን ውድቅ እንደሚያደርጉ ዳኛው አሳውቀዋት ነበር።

በዚምባብዌ ሕግ መሠረት መንግሥቱ ክሥ የሚመሠርትበትን ቀን ካሳወቀ የተከሳሹን የዋስትና መብቷን አንስቶ መልሶ ሊጠራ ይችላል።

የዚምባብዌ ጦር ሙጋቤን አስወግዶ ምክትላቸው የነበሩትን ኤመርሰን ምናንጋጓን ለፕሬዚዳንትነት የሰየመው ማርታ ከታሠረች ከጥቂት ሣምንታት በኋላ ነበር።

ማርታ የምትሠራበት ማጋምባ ቴሌቪዥን የፖለቲካ ስላቆችና አስቂኝ ፕሮግራሞችን እየሠራ የሚያወጣ አነስተኛ የሚድያ ኩባንያ ነው።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

ሙጋቤን ዘልፈሻል የተባለች አሜሪካዊት ነፃ ወጣች
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:35 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG