የሩሲያ ኃይሎች ትናንት ሌሊቱን በተለየዩ የዩክሬን አካባቢዎች ላይ የአየር ጥቃት አድርሰዋል። ሩሲያ በኢራን የተሰሩ ድሮኖችን በይበልጥ በመጠቀም ላይ ነች ሲሉ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንሲኪ አስጠንቅቀዋል።
የሩሲያ ሚሳይሎች እና መድፎች በኋለኛው ጥቃት የምስራቅ ዶኔትስካና ካርኪቭ አካባቢዎችን መምታታቸውን የዩክሬን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
ዜሌንስኪ በትናንት ማታ ንግግራቸው ሩሲያ በቅርብ ወራት እየተጠቀመችባቸው ባሉት ኢራን ሰራሽ ሚሳይሎች በዩክሬን ዙሪያ ለረጅም ጊዜ ማጥቃቷን ለመቀጠል ስለማቀዷ መረጃ አግኝተናል ብለዋል።
በሌላ በኩል ትናንት ሰኞ ሩሲያ ባወጣችው መግለጫ በያዘችው በምስራቅ ዶኔትስክ ግዛት ማኪቫ ከተማ ካምፕ ውስጥ የነበሩ 63 ወታደሮቿ በዩክሬን የሚሳይል ጥቃት እንደተገደሉባት ተናግራለች።
የዩክሬን የጦር ኃይሎች አዛዥም ጥቃቱ መድረሱን ትናንት ያረጋገጡ ሲሆን በከተማዋ የነበሩ 10 የሩሲያ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች አውድመናል ወይም ጉዳት አድርሰንባቸዋል ሲሉ መናገራቸው ተጠቅሷል፡፡