በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጉቴሬሽና ኤርዶዋን ዩክሬን ናቸው


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽና የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬቼፕ ታዪፕ ኤርዶዋን ዛሬ ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጋር ምዕራባዊቱ ልቪቭ ከተማ ውስጥ ተገናኝተው እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

ውይይታቸው በዓለምአቀፉ የምግብ ቀውስ፥ በኒኩሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ ስለተደቀኑ አደጋዎችና ሩሲያ እያካሄደች ያለችው ጦርነት ሊቆም በሚችልባቸው ሁኔታዎች ላይ እንደሚያተኩር ተነግሯል።

ዓለምአቀፉን የምግብ ቀውስ ለማቃለል ጥረቱ የቀጠለ ሲሆን የመንግሥታቱ ድርጅትና ቱርክ ባሸማገሉት ስምምነት መሠረት ካለፈው ሃምሌ 25 ጀምሮ ሃያ አራት መርከቦች እህል እየጫኑ ከዩክሬን መውጣታቸው ተገልጿል።

ጉቴሬሽ ነገ፤ ረቡዕ ኦዴሳ ወደብን እንደሚጎበኙና ቅዳሜ ደግሞ ወደ ኢስታንቡል እንደሚጓዙ፤ በዚያም ከዩክሬይን እህል የሚጓጓዝበትን ሥርዓት የሚቆጣጠረውን የጋራ ቅንጅት ማዕከል እንደሚጎበኙ ታውቋል።

ይህ በዚህ እንዳለ በሩሲያ በተያዘችው ክሬምያ ልሳነምድር ባለፈው ሣምንት በተከታታይ የደረሱት የቦምብ ፍንዳታዎች ‘ኃይሎቻችን ያወጡት አዲስ የውጊያ ስልት አካል ነው’ ሲሉ አንድ የዩክሬን ባለሥልጣን ተናግረዋል።

ሩስያ ጥቃቶቹን "አሻጥር" ብላ አውግዛለች።

ስማቸው ያልተገለፀ አንድ የዩክሬን ባለሥልጣን ለዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ በሰጡት ቃል ክርምያ ላይ ጥቃቱን ያደረሱት ልዩ ኃይሎቻችን መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ ባለፈው ሣምንት ክሪምያ በሚገኘው የሩሲያ የአየር ኃይል ሠፈር ላይ ከተፈፀመውና ዘጠኝ የጦር ጄቶችን ካወደመው ጥቃት በኋላ ባደረጉት ንግግር "ጦርነቱ ክሪምያ ላይ ተጀምሯል፤ ክሪምያን ነፃ በማውጣት ይጠናቀቃል" ብለው ነበር።

XS
SM
MD
LG