የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ የአለም መሪዎች ፈርጀ ብዙውን ግቦች ለማሳካት እንዲሰሩ በማሳሰብ ዛሬ ማክሰኞ የመንግስታቱን ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ከፍተዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር ለ2030 ከተያዙት 17ቱ የዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ 15 በመቶው ብቻ ለስኬት ከሚያበቃ ጎዳና ላይ ናቸው ያሉት ጉቴሬሽ፣ የአለም ማህበረሰብ እንኚህን ግቦች ለማሳካት “ወደ አንድ መምጣት የማይችል” መስሎ በመታየቱ ማዘናቸውን ተናግረዋል።
“እድገትን ለማፋጠን መንግስታት ተጨባጭ እቅዶችን እና ሀሳቦችን ይዘው ወደ ውይይቱ ጠረጴዛ የሚቀርቡበት ጊዜ ነው”
ጉቴሬሽ አያይዘውም፡ ማንንም ከኋላ ትተን ከመጓዝ ይልቅ፣ እነኝህን ግቦች ጥለን ልንመጣ ከምንችልበት አደጋ ላይ ነን” ብለዋል። “አሁንም እነኝህን ግቦች መታደግ የሚያስችል ዓለም አቀፍ ዕቅድ ያስፈልገናል” ሲሉ ጉቴሬሽ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ጉባኤው “እድገትን ለማፋጠን መንግስታት ተጨባጭ እቅዶችን እና ሀሳቦችን ይዘው ወደ ውይይቱ ጠረጴዛ የሚቀርቡበት ጊዜ ነው” ብለውታል።
እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2015 የተቀመጡት እና በመጭው ሰባት አመታት ውስጥ ለማሳካት የዓለሙ ድርጅት የያዛቸው ግቦች፡ ለድህነት እና ረሃብን ማብቂያ ማበጀት፣ በተመጣጣኝ ዋጋ የኃይል አቅርቦት ማግኘት መቻልን ማረጋገጥ፣ የአየር ንብረት ለውጥን በብቃት ለመዋጋት የሚያስችሉ አፋጣኝ እርምጃዎችን መውሰድ እና የፆታ እኩልነትን ማስፈን” የሚሉት ይገኙበታል።
በዛሬው የጠቅላላ ጉባኤው መክፈቻ ከዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባይደን እና ከዩክሬይኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በተጨማሪ፡ የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ዳ ሲልቫ፣ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን፣ የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ እና የኢራን ፕሬዝዳንት ራይሲ፡ ይናገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
መድረክ / ፎረም