በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሽብር ተጠርጣሪው ዮናታን መላኩ በእሥር ላይ ነው


ዮናታን መላኩ
ዮናታን መላኩ

በዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ መሥሪያ ቤት አቅራቢያ ባለፈው ሣምንት በደረሰው የፀጥታ ሽብር ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለው ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊ ትላንት ፍርድ ቤት ቀርቦ በወታደራዊ ተቋማት ሕንፃዎች ላይ በመተኰስ ወንጀል ክስ ተመሥርቶበታል።

የ 22 ዓመቱ ዮናታን መላኩ የዩናይትድ ስቴትስ ባህር ኃይል ተጠባባቂ ወታደር ሲሆን ባለፈው ሣምንት ተይዞ የታሠረው አርሊንግተን፣ ቨርጂንያ በሚገኘው ብሔራዊ መካነ መቃብር ሕግ ጥሶ ከገባ በኋላ ፖሊስ እንዲቆም ሲጠይቀው ለማምለጥ ሲሞክር ነው።

ፖሊስ ባለፈው ዓርብ በትውልድ ኢትዮጵያዊውን አሜሪካዊ ዮናታን መላኩን በመጠርጠር በቁጥጥር ሥር ለማዋልና ወደ ፔንታገን የሚያመራውን አውራ መንገድ ዘግቶ ጥልቅ ምርመራ ለማካሄድ የወሰነው በግለሰቡ አድራጎትና በወቅቱ ይዞ በነበረው ቁሳቁስ ምክንያት ነው።

የፌዴራሉ ዓቃብያነ ሕግ ትላንት ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የክስ ማመልከቻም ዮናታን በወቅቱ ይዞት ከነበረው ታዛይ ቦርሣ ውስጥና ኋላም መኖሪያ ቤቱ ሲፈተሽ ናይትሬት የተባለ ለቦንብ መሥሪያ ሊውል የሚችል ንጥረ-ነገር ማግኘታቸውን ዘርዝረዋል።

በመኪና የተፃፈ ፈንጂ መሥሪያ ቁሳቁስ ዝርዝር ያለበት ሰነድ ማግኘታቸውንም አስረድተዋል።

መርማሪዎች አክለውም ዮናታን መላኩ በባህር ኃይሉ ብሄራዊ ሙዚየም ሕንፃ ላይ ሲተኩስ እንዲሁም በተደጋጋሚ በአረብኛ ቋንቋ «አላህ ወአክባር» ወይም «አላህ ታላቅ ነው» እያለ ሲፈክር የሚያሳይ እራሱን የቀረጸበት ቪዲዮ ማግኘታቸውንም አብራርተዋል።

ቪዲዮው በተጨማሪም ዮናታን ከመኪናው ውስጥ ሆኖ እየተኮሰ «የሚያገኙት ይህንን ነው። ዒላማዬ ይሄ ነው። ይህ የወታደራዊ ሕንፃ ነው። ጥቃት ይደርስበታል» እያለ ሲናገር ያሳያል ተብሏል።

በዩናይትድ ስቴትስ ባህር ኃይል ቃል አቀባይ መግለጫ መሠረት ዮናታን መላኩ ሲቀጠር ኃይማኖቱን ያስመዘገበው ሙስሊም ነኝ ብሎ ነው። እስከዛሬ በየትኛውም ጦር ግንባር ተመድቦ ባያውቅም ዮናታን በተጠባባቂነት ተመዝግቦ የሚገኝ ያሜሪካ ወታደር ነው።

ዝርዝሩን ያዳምጡ

XS
SM
MD
LG