በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሁቲዎች ጥቃት የደረሰበት የእንግሊዝ የጭነት መርከብ መስመጡን የመን አስታወቀች


ፎቶ ፋይል፡ ይህ ፎቶ እአአ የካቲት 27/2024 የተነሳ ሲሆን ሩቢማር የጭነት መርከብ በየመን የባህር ዳርቻ መስጠሟን ያሳያል፡፡
ፎቶ ፋይል፡ ይህ ፎቶ እአአ የካቲት 27/2024 የተነሳ ሲሆን ሩቢማር የጭነት መርከብ በየመን የባህር ዳርቻ መስጠሟን ያሳያል፡፡

ባለፈው ወር በሁቲዎች ጥቃት የደረሰበት እና ንብረትነቱ የእንግሊዝ የሆነው ሩቢማር የጭነት መርከብ መስመጡን ዓለም አቀፍ እውቅና ያላው የየመን መንግሥት ቅዳሜ እለት አስታውቋል።

የሁቲ ታጣቂዎች በህዳር ወር የንግድ መርከቦችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ከጀመሩ ወዲህ ሙሉ ለሙሉ የወደመ የመጀመሪያው መርከብ ነው።

የየመን መንግስት ባወጣው መግለጫ፣ መርከቧ አርብ ምሽት በደቡባዊው የቀይ ባህር ክፍል መስመጧን አስታውቆ ከፍተኛ "የአካባቢ ብክለት" ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቋል።

መርከቡ ጥቃት በደረሰበት ወቅት ከ41 ሺህ ቶን በላይ ማዳበሪያ ጭኖ እንደነበር የዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ ማዕከላዊ ዕዝ አስታውቋል።

ሁቲ ጥቃቶቹን የሚያካሂደው በጋዛ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን አጋርነቱን ለማሳየት እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገልፃል።

የየመን መንግሥት ሰኞ እለት የእንግሊዝ ንብረት የሆነውን ሩቢማር የጭነት መርከብ የጎበኘ ሲሆን በከፊል መስመጡን እና በጥቂት ቀናት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ሊሰምጥ እንደሚችል አመልክቷል።

የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ቀደም ሲል ጥቃቱ መርከቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ እና 18 ማይል የሚሆነው ነዳጅ እንደሰመጠ አስታውቆ ነበር።

የሁቲ ጥቃቶች የመርከብ ኩባንያዎች መንገዳቸውን እንዲቀይሩ እና ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣውን የደቡብ አፍሪካ መስመር እንዲጠቀሙ ያስገዳቸው ሲሆን፣ በቀይ ባህር የኤደን ባህረሰላጤ እና ባብ አል-ማንዳብ ወይም 'ጌት ኦፍ ቲርስ' በሚባለው መተላለፊያ ሰርጥ መርከቦች ላይ እየደረሰው ላለው ጥቃት፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና እንግሊዝ ከጥር ወር ጀምሮ በሁቲዎች ላይ የበቀል ጥቃት እያካሄዱ ነው።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG