የየመንን ሰሜናዊ ምዕራብ ክፍል የተቆጣጠሩትና ከኢራን ጋራ ያበሩት የሁቲዎች ቡድን አባላት፣ ወደ እስራኤል የተኮሷቸውን ሚሳዬሎች እና የላኳቸውን ድሮኖች የቪዲዮ ምስል፣ ዛሬ ረቡዕ ይፋ አድርገዋል፡፡
የቡድኑ ወታደራዊ ብዙኀን መገናኛ፣ ዛሬ ባሰራጨው ተንቀሳቃሽ ምስል፥ በርካታ ባለስቲክ፣ ባለ ክንፍ ሚሳኤሎች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች(ድሮኖችን) አሳይቷል፡፡
ሁቲዎች፣ በኃይል ከተቆጣጠሩት ሰነዓ፣ አንድ ሺሕ ማይል ርቆ በሚገኘው የእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት ውስጥ በመሳተፍ፣ ትላንት ማክሰኞ፣ ወደ እስራኤል ሚሳዬሎችን መተኮሳቸው እና ድሮኖችንም መላካቸው፣ የግጭቱን ቀጣናዊ አደጋ አጉልቶ ያሳያል፤ ተብሏል፡፡
ሐማስ፣ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 7 ቀን፣ በእስራኤል ላይ ጥቃት ካደረሰበት ጊዜ ጀምሮ፣ ሁቲዎች ፍልስጥኤማውያንን በመደገፍ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡
የሁቲዎች ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያኽያ ሰአሬ፣ ትላንት ማክሰኞ በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ፣ ቡድኑ፣ በርካታ የባለስቲክ ሚሳዬሎችንና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ወደ እስራኤል መተኮሳቸውንና መላካቸውን አስታውቀዋል፡፡
የፍልስጥኤማውያንን ድል ለመደገፍ፣ ሌሎች ተመሳሳይ ጥቃቶች እንደሚቀጥሉም፣ ቃል አቀባዩ አክለው ተናግረዋል፡፡
ሁቲዎች፣ በየመን ጦርነት፣ በሳዑዲ አረቢያ እና በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ላይ ባደረሱት ጥቃት፣ በሚሳዬል እና በሰው አልባ አውሮፕላኖች ያላቸውን የተኩስ ዐቅም አሳይተዋል።
በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት፥ ሁቲዎችን በማስታጠቅ፣ በማሠልጠንና በገንዘብ በመደገፍ፣ ኢራንን ከሷል።
የእስራኤል ዋና አጋር የኾነችው ዩናይትድ ስቴትስ፣ የጋዛ ግጭት እንዳይስፋፋ ለመከላከል፣ አየር ማጓጓዣዎችን ወደ ቀጣናው አሰማርታለች።
መድረክ / ፎረም