የመን ውስጥ ከሚካሄደው ግጭት ጋር ተያይዞ የሚካሄደው የእስረኞች ልውውጥ መጀመሩ ተነገረ።
ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በሁቲ አማጽያንና በሳዑዲ አረብያ በሚመራው የቅንጅት ኃይሎች በሚደገፈው መንግሥት መካከል የሚካሄደው የእስረኞች ልውውጥ ዛሬ ዓርብ መጀመሩን አስታውቋል። እስረኞቹን የጫነው የመጀመሪያው አውሮፕላን በአማጽያን ቁጥጥር ስር ካለችው ሰነዓ በመንግሥት ቁጥጥር ወዳለችው ኤደን መጓዙንም ኮሚቴው ገልጿል።
በመጭዎቹ ቀናት ከሁለቱም ወገኖች ቁጥራቸው ወደ 900 የሚጠጉ እስረኞች የሚለቀቁ ሲሆን የእስረኞቹ ልውውጥ እየተካሄደ ያለው ባለፈው ወር ስዊዘርላንድ ላይ የተደረገውን ድርድር ተከትሎ ነው።
በሳዑዲ አረብያና በኢራን መካከል የሚካሄድ የውክልና ጦርነት ተደርጎ በሚታሰበው በየመኑ ግጭት፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ሚሊዮኖች ደግሞ ለረሃብ ተጋልጠዋል።
ሳዑዲ መሩ ጥምረት፣ በየመን ጦርነት ጣልቃ መግባት የጀመረው እአአ በ2015 ሲሆን፣ በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማጽያን እአአ በ2014 የየመን መንግሥትን ከሰነዓ ካባረሩ በኋላ መሆኑ ተመልክቷል።