በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለ16 ሚሊዮን የመናውያን የ3.5 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ተጠየቀ


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንተኒ ጉተሬዝ እኤአ 2019 በየመን ለተፈጠረው የሰብአዊ ቀውስ የእርዳታ ማሰባሰቢያ ጥሪ ሲያደርጉ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንተኒ ጉተሬዝ እኤአ 2019 በየመን ለተፈጠረው የሰብአዊ ቀውስ የእርዳታ ማሰባሰቢያ ጥሪ ሲያደርጉ፡፡

የተባበሩት መንግስታት በጦርነት ግጭት እየታመሰች በምትገኘው የመን ህይወታቸውን ለማትረፍ ለሚጣጣሩ 16 ሚሊዮን ሰዎች የሚውል የ3.85 ቢሊዮን እርዳታ እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ “ምንም የምናባክነው ጊዜ የለንም” ይላሉ፡፡

“ረሀብ በየመን ላይ እየወረደ ነው፡፡ በዚህ ዓመት 16 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የሚላስ የሚቀመስ አይኖራቸውም፡፡ ገና ከወዲሁ እንኳ 50 ሺ የሚሆኑ የመናውያን ህይወታቸው ከሚነጥቀው የረሀብ አደጋ ላይ ወድቀዋል፡፡”

ዋና ጸሀፊው፣ በበአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ እጅግ የከፋው ይህ ሰብአዊ ቀውስ በህጻናት ላይ እየተገለጸ ነው በማለት እንዲህ ይላሉ

“ዛሬ በየመን ህጻን ሆኖ መገኘት ማለት በተለየ ገሃነም እንደመገኘት ነው፡፡ የየመን ህጻናት ታርዘዋል፡፡ በዚህ ዓመት ወደ ግማሽ የሚጠጉት የየመን ህጻናት ከምግብ እጦትና ከሱም ጋር ተያይዞ በሚመጣው ህመም ይሰቃያሉ፡፡ ድካም ድብርትና የመሳሰሉት ምልክቶችም ይታይባቸዋል፡፡ ከእነዚህ ህጻናት መካከል 400ሺ የሚሆኑት በሚጋያጋጥማቸው ከባድ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተነሳ አስቸኳይ ህክምና ሳያገኙ ሊሞቱ ይችላሉ፡፡”​

ለ16 ሚሊዮን የመናውያን የ3.5 ቢሊዮን እርዳታ ተጠየቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:31 0:00

ጦርነቱ ከተጀመረበት፣ እኤአ ከ2014 ጀምሮ፣ ከ18ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሞተዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባወጣው ዘገባ፣ ሁለት ሺ የሚሆኑ ሰላማዊ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፣ ወይም የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

ጉተሬዝ ጦርነቱ መላውን የየመን ትውልድ ሊውጥ ይችላል በማለት ያስጠነቅቃሉ፡፡ ስለሆነም “መቆም አለበት” ይላሉ፡፡

በዚህ መካከል ግን፣ እሳቸው እንደሚሉት፣ በየመን ቢያንስ ከሶስት ሰዎች ሁለቱ የምግብ፣ የጤና ወይም የህይወት ማሰንበቻ እርዳታ ይፈልጋሉ፡፡

“እነዚህ አጣዳፊ እርዳታዎች የሚያስፈልጉት ደግሞ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እርዳታ ከእስከዛሬዎቹ ሁሉ እጅግ ዝቅተኛ በሆነበት ሰዓት ነው” ብለዋል፡፡

ዋና ጸሀፊው በአለፈው ዓመት ከተጠየቀው 1.9 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ውስጥ እስካሁን የተገኘው ግማሽ ያህሉ ብቻ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ እሱም ቢሆን ደግሞ ከሱ በፊት ከነበረው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በግማሽ ያነሰ ነበር ብለዋል፡፡

“እርዳታ መቀነስ ማለት በጠቅላላው ቤተሰብ ላይ የሞት ፍርድ እንደመበየን ነው” ይላሉ ጉተሬዝ፡፡

“ይህ ከየመን ጉዳይ ወደኋላ የምንልበት ጊዜ አይደለም፡፡ እኤአ በ2018 ካገኘነው እኩልና እንዲያውም ከዚያም ያለፈ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት ይኖርብናል፡፡ ረሀብ አገሪቱን ከመዋጡ በፊት ለጋሽ አገሮች ተማጽኖአችንን ሰምተው እንዲደግፉን እጠይቃለሁ፡፡ እያንዳንዷ ዶላር ትጠቅማለች፡፡”

ዩናይትድ ስቴትስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊን ተማጽኖ ሰምታለች፡፡ ምክንያቱም ለተማጽእኖው የመጀመሪያውን ምላሽ የሰጡት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ናቸው፡፡

እንዲህ አሉ ብሊንከን

“ዛሬ ለሰብአዊ እርዳታ የሚውል ወደ 191 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ተጨማሪ ገንዘብ ከዩናይትድ ስቴትስ ማግኘታችንን ስገልጽ በደስታ ነው፡፡ ይህም የ2021 ዓመት በጀታችንን ወደ 350ሚሊዮን ዶላር ያሳድግልናል፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ ቀውሱ ከጀመረበት የዛሬ ስድስት ዓመት ጀምሮ፣ ለየመን ህዝብ ከ3.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ እርዳታ ሰጥታለች፡፡”

ብሊንከን ሌሎች አገሮችም በተለይም በቀጠናው ያሉት አገሮች በቸርነት እርዳታቸውን እንዲለግሱ ጠይቀዋል፡፡ አያይዘውም “ኮቪድ 19 ከሱም ጋር ያለው የኢኮኖሚ ቀውስ የሰብ አዊ መብት ቀውሶችን የበለጠ ስላባባሰው እርዳታችንን በአጠፋኝ መስጠት ይኖርብናል” ብለዋል፡፡

(የቪኦኤ ዘጋቢ ሊሳ ሽላይን ከጀኔቭ ከላከችው ዘገባ የተወሰደ፡፡)

XS
SM
MD
LG