ካይሮ —
ፍልሰተኞችን የያዙ አራት ጀልባዎች በየመንና ጂቡቲ ባህር ዳርቻ ሰምጠው ቢያንስ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ 186 የሚሆኑት የደረሱበት እንደማይታወቅ የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) አስታውቋል።
አደጋው የደረሰው ትላንት ሐሙስ ምሽት ሲኾን፣ በባህረ ሰላጤው ሀገራት ሥራ ለማግኘትና ከግጭት ለመሸሽ ኢትዮጵያን በሚጠቀሙበት የጉዞ መሥመር ላይ እንደኾነም የአጃንስ ፍራንስ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።
በየመን ዳርቻ ከሰመጡት ጀልባዎች በአንደኛው ላይ 150 ኢትዮጵያውያንና አራት የጀልባው ሠራተኞች ተሳፍረው የነበረ ሲሆን፣ በሌላኛው ጀልባ ላይ ደግሞ 31 ኢትዮጵያውያንና ሦስት የመናውያን የጀልባው ሠራተኞች ተሳፍረው እንደነበር ታውቋል።
አሶስዬትድ ፕረስ በበኩሉ በየመን ዳርቻ የሰመጡት ሁለት ጀልባዎች ሠራተኞች ከአደጋው ሲድኑ፣ 181 ፍልሰተኞችና አራት የመናዊ የጀልባዎቹ ሠራተኞች የደረሱበት እንዳልታወቀ ዘግቧል።
በጅቡቲ ባህር ዳርቻ ሁለት ጀልባዎች በተመሳሳይ ሰዓት መስመጣቸውንና፣ የሁለት ፍልሰተኞች አስከሬን ሲገኝ የተቀሩትን መታደጋቸውን የአይ ኦ ኤም ቃል አቀባይ ታሚም ኢሌይን አስታውቀዋል።
በጅቡቲ ባህር ዳርቻ የደረሰው አደጋ ምክንያት ከፍተኛ ኃይል ያለው ነፋስ በመከሰቱ እንደኾነም ተጠቁሟል።
መድረክ / ፎረም