በየመን ከሚገኙት ሁቲ አማፂያን የተላከ ኢራን ሰራሽ ድሮን በቴል አቪቭ፣ እስራኤል አንድ ሰው ገድሎ አስር ሌሎችን አቁስሏል።
ጥቃቱ በማዕከላዊ ቴል አቪቭ በአሜሪካ ኤምባሲ አቅራቢያ ሲደርስ፣ ስለት ያላቸው ነገሮችን አና የመስታወት ስብርባሪዎች እንዲዘንብ አድርጓል።
የሁቲ አማፂያን ለጥቃቱ ወዲውኑ ኃላፊነት ወስደዋል።
በእስራኤል ሁለተኛ ትልቋ ከተማ ላይ የደረሰው ጥቃት አስገራሚ ነው ተብሏል። ይኽውም እስከ ዛሬ ከሁቲ ይላኩ የነበሩ ድሮኖችና ይተኮሱ የነበሩ ሚሳዬሎች በእስራኤል መከላከያ ተመተው ይወድቁ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ዓርብ የተላከው ድሮን ግን በርካታ የእስራኤል ተደራራቢ የመከላከያ ስርዓቶችን አልፎ ቴል አቪቭ በመድረሱ ነው።
የእስራኤል ሠራዊት ምን ስህተት ተፈጽሞ እንደነበር ምርመራ ላይ እንደሆነ አስታውቋል።
የሁቲ አማፂያን አዲሶቹ ድሮኖች የእስራኤልን መከላከያ ሥርዓቶች ጥሰው እንደሚያልፉ አስታውቀው ነበር።
የድሮኑ ጥቃት የተፈጸመው እስራኤል በጋዛ ላይ ለምታደርገው ጦርነት በቀል እንደሆነ የሁቲ አማፃያኑ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ አስታውቀዋል።
ድሮኑ ረጅም ርቀት ተጓዡ ሳማድ-3 የተባለው ኢራን ሰራሽ መሆኑንና ከየመን እንደተነሳም እንደደረሰበት የእስራኤል ሠራዊት አስታውቋል።
መድረክ / ፎረም