በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የየመን ሁቲ አማጺያን ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ከሀገራቸው አባረሩ፣ በርካታዎችን ገደሉ


 የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ሂውማን ራይትስ ዎች ትላንት ካወጣው መግለጫ ጋር አብሮ ካያያዘው ቪዲዮ ላይ የተወሰደ ምስል
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ሂውማን ራይትስ ዎች ትላንት ካወጣው መግለጫ ጋር አብሮ ካያያዘው ቪዲዮ ላይ የተወሰደ ምስል

የየመን ሁቲ አማጺያን በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ከሀገራቸው ለማስወጣት በከፈቱት ተኩስ በርካታ ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ሂውማን ራይትስ ዎች ትላንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የተኩስ ጥቃቱን ለማምለጥ ወደ ሳውዲ ድምበር ለመግባት የሞከሩ በርካታ ስደተኞች ላይ የሳውዲ ድምበር ጠባቂ ወታደሮች ተኩስ በመክፈታቸው ተጨማሪ ኢትዮጵያኖች መሞታቸውንም መግለጫው አካቷል።

የየመን ሁቲ አማጺያን ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ከሀገራቸው አባረሩ፣ በርካታዎችን ገደሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:08 0:00

በሳውዲ እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች በበኩላቸው በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ መሆናቸውንና ወደ ሀገራቸው መመለስ እንደሚፈልጉ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

መግለጫው እንደሚያስረዳው በየመን ሰሜናዊ ክልል ከሳውዲ ጋር በሚያዋስነው አል ጋሀር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በድንኳን ተጠልለው ይኖሩ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ ስደተኞች፣ አካባቢውን በሚቆጣጠረው የሁቲ አማፂያን ቡድን ተገደው ወደ ሳውዲ አረቢያ ድምበር እንዲሄዱ የተደረጉት ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር ነበር።

ከተባራሪ ስደተኞቹ አንዱ፣ በየመን ድምበር ላይ ለአንድ አመት የኖረው በላይ አብርሃ ነው። የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከሀገሩ እንደወጣና ወደ ሳውዲ አረብያ ለመግባት የተሻለ ግዜ እየጠበቀ እንደነበር የሚናገረው በላይ፣ የሁቱ አማፂያኑ በድንገት መጥተው እንዳባረሯቸው ያስረዳል።

አማፂያኑ ስደተኞቹ ይኖሩባቸው የነበሩትን ከ 300 በላይ ድንኳኖች በማፈራረስና በጠመንጃ አፈ-ሙዝ በማስፈራራት ኢትዮጵያኖቹን ያባረሯቸው የኮሮና ቫይረስ አለባቸው በሚል ሽፋን መሆኑን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ሂዩማን ራይትስ ወች ትላንት ባወጣው መገለጫ አስታውቋል። መግለጫው አክሎ አማፂያኑ ስደተኞቹ ላይ ተኩስ በመክፈት ለግዜው ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ ኢትዮጵያውያንን መግደላቸውንም ከአይን እማኞች ማረጋገጡን ገልጿል።

የድርጅቱ የስደተኞችና ፍልሰተኞች መብት ዳይሬክተር የሆኑት ቢል ፍሬሊክ ለአሜሪካ ድምፅ እንደገለፁት ኢትዮጵያኖቹ ከሁቱ አማፂያኖች ጥቃት በመሸሽ ወደ ሳውዲ ድምበር ለመግባት ሲሞክሩ የሳውዲ ድምበር ጠባቂ ወታደሮች ተኩስ በመክፈታቸው ተጨማሪ ኢትዮጵያውያን ለህልፈት ተዳርገዋል።

ስደተኞቹ ሰፍረውበት የነበረው አል ጋሀር የተሰኘው አካባቢ ብዙዎች ወደ ሳውዲ ለመሻገር የሚጠቀሙት የስደት መንገድ ነው። ለስደተኞች ምንም አይነት ከለላ የማይሰጠው የሳውዲ መንግስት ግን ወደ ሀገሩ በህገወጥ መንገድ የሚገቡ ስደተኞችን አስሮ ወደ ሀገራቸው የሚመልስ ሲሆን በኮቪድ 19 ምክንያት የአየር በረራዎች በመቋረጣቸው ግን በርካታ ስደተኞች በእስር ለመቆየት ተገደዋል።

ሳውዲ ውስጥ ጂዛን በተሰኘ እስር ቤት ውስጥ የሚገኘው በላይ እሱና ሌሎች ከ 14 ሺህ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊ ስደተኞች በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ እንዳሉና ከ መቶ ሰው በላይ በማይዙ ክፍሎች ውስጥ እስከ 400 የሚሆኑ ታሳሪዎች በአንድ ላይ መታጎራቸውን ገልፆ፣ ብዙ ሰዎች በተላላፊ በሽታና በጭንቀት እየሞቱ ነው ይላል።

ኢትዮጵያዊያኖቹ በሳውዲ ወታደራዊ ካምፖች ውስጥ በአስከፊ ሁኔታ በእስር ላይ መሆናቸውን ሂዩማን ራይትስ ወችም ማረጋገጡን ፍሬሊክ ያስረዳሉ ።

በሳውዲ እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለሂዩማን ራይትስ ወች ቀርፀው በላኳቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች ኢትዮጵያውያኖቹ በጠባብ እና ሞቃታማ ክፍሎች ውስጥ በቆሻሻ መሀል ታጭቀው ይታያሉ። ከሽንት ቤት የሚወጣ ፍሳሽ በቀላቀለ ውሃ መሃል ተቅምጠው፣ ድረሱንልን እያሉ ሲጮሁም ይሰማሉ።

የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገርናቸው ኢትዮጵያውያንም ነፍሰ ጡር እናቶችን ጨምሮ በእስር ቤቶቹ ውስጥ ያሉት ስደተኞች በቂ ምግብና ውሀ እንዲሁም ህክምና እንደማያገኙ፣ የሚለብሱት ልብስና የሚተኙበት ፍራሽ እንደሌላቸውና፣ በሳውዲ ጠባቂዎች ድብደባ እንደሚደርስባቸው ነግረውናል። 

የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገርናቸው ኢትዮጵያውያንም ነፍሰ ጡር እናቶችን ጨምሮ በእስር ቤቶቹ ውስጥ ያሉት ስደተኞች በቂ ምግብና ውሀ እንዲሁም ህክምና እንደማያገኙ፣ የሚለብሱት ልብስና የሚተኙበት ፍራሽ እንደሌላቸውና፣ በሳውዲ ጠባቂዎች ድብደባ እንደሚደርስባቸው ነግረውናል።

ከነዚህ መሃል ሻምበል ከበደ ሌላው በጂዛን እስር ቤት የሚገኝ ታሳሪ ነው። በወሎ፣ ራያ ከተማ ነዋሪ የነበረው ሻምበር እንደ አብዛኛው ስደተኛ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ካገሩ ቢወጣም እስካሁን ከስቃይ በቀር ያጋጠመን የለም፣ ስለዚህ ወደ ሀገራችን መመለስ እንፈልጋለን ይላል።

ፍሬሊክ፣ ድርጅታቸው በእስረኞቹ ላይ እየደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከት የሳውዲ መንግስትንና በየመን ሰሜናዊውን ክፍል የሚቆጣጠረውን የሁቲ አማፂያንን ለማነጋገር ሞክሮ እስካሁን ምላሽ እንዳላገኘ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች በሁቱ አማፂያንና በሳውዲ ወታደሮች ጥቃት ከደረሰባቸው ኢትዮጵያኖች በተጨማሪ የኤርትራና የሶማሌ ስደተኖች ሊኖሩ ይችላሉ ብሎ ቢገምትም እስካሁን ያገኛቸውና ያናገራቸው ግን ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ገልጿል። ድርጅቱ ባለፈው አመት ያሰባሰበው መረጃ እንደሚያመለክተው በኢኮኖሚ ችግር፣ በድርቅና በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት በየመን አቋርጠው ወደ ሳውዲ ከሚጏዙ ስደተኞች መሀል 90 በመቶው ኢትዮጵያውያን ናቸው። አለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅትም በ 2019 ዓ.ም. ብቻ ከ 140 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች የመን መግባታቸውን ጠቁሟል።

(ሙሉ ዘገባውን ከድምፅ ፋይሉ ያዳምጡ)

XS
SM
MD
LG