በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በደቡብ አፍሪካ ንብረታቸውን በዘራፊዎች የተቀሙ ሁለት ኢትዮጵያውያን ይናገራሉ


ናይጄሪያዊ በደቡብ አፍሪካውያን ጥቃት ሲደርስበት/02/18/17
ናይጄሪያዊ በደቡብ አፍሪካውያን ጥቃት ሲደርስበት/02/18/17

በደቡብ አፍሪካ ከሁለት ዓመት በኋላ በድጋሚ ባገረሸው በመጤዎች ጥላቻ ላይ ያነጣጠረ ዝርፊያ ፕሪቶሪያ "አትረጅቪል" በተባለች መንደር ውስጥ ሙሉ የሱቅ ንብረታቸውን እንደተሰረቁ ሁለት ኢትዮጵያውያን ለአሜሪካ ድምጽ ተናገሩ። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ሱቃችን ሲዘረፍ ይሄ ሁለተኛ ጊዜያቸው እንደሆነ የተናገሩት ነጋዴዎች “ሱቆቹን ያሟላነው ተበድረን ነበር። ዕዳውን ሳንከፍል ከነቤተሰቦቻችን ቧዶ እጃችንን ቀረን ብለዋል።”

ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆኑት ወንጌላዊ ሀብታሙ ፀጋዬ ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ መኖር ከጀመሩ ዐስር ዓመት ሆኗቸዋል። መኖሪያ ቤታቸው በከተማዋ መሀል “ሰኒ ሳይድ” በተባለ ቦታ ነው። የንግድ ቦታቸው የሚገኘው ደግሞ ከመኖሪያ ቤታቸው 20 ኪሎሜትር ርቆ በሚገኘ “አትረጅቪል” በተባለች መንደር ውስጥ ነበር።

በደቡብ አፍሪካ ንብረታቸውን በዘራፊዎች የተቀሙ ሁለት ኢትዮጵያውያን
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:00 0:00

አርብ የካቲት 17/2009 ዓ.ም ራሳቸውን “የማሚሎዲ ሁኔታ ያሳስበናል” ብለው የሚጠሩ ማሚሎዲ በተባለች የድሆች መኖሪያ ሰፈር የሚኖሩ ደቡብ አፍሪካውያን ነዋሪዎች በአንድ ላይ ሕብረት በመፍጠር፤ “መጤዎች ከሀገራችን ይውጡልን፤ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች መሥሪያቤት ለመጤዎቹ የፍቃድ ወረቀት ማደስ ያቁም” የሚል መሪ መፈክር ይዘው የተቃውሞ ሰልፍ ሊወጡ መሆኑ ተሰማ።

ለተቃውሞ በተበተነው በራሪ ወረቀት ላይ 34 በመቶ የሚሆኑ ደቡብ አፍሪካውያን ሥራ ዕጥ ሆነው መጤዎቹ ግን ባለስራና ባለሀብት ናቸው የሚል መልዕክትም ሰፍሮበታል።

ወንጌላዊ ሀብታሙ ይህን ሰልፍ ተገን በማድረግም ዝርፊያ ሊኖር እንደሚችል መረጃ ስለደረሳቸው ከእሳቸው ጋር በአካባቢው ሱቅ ያለውን ነጋዴ እና ሌሎች ሊረዷቸው የሚችሉ አምስት ኢትዮጵያውያን አስከትለው ንብረታቸውን ከሱቃቸው አውጥተው ለማሸሽ ወደዚያው አመሩ። በቦታው ሲደርሱ "ሰቮና ሱፐርማርኬት" የተባለውና የሱቁ ቁጥር 45 የሆነው የሸቀጣ ሸቀጥ መሸጫቸው እንዳለ መዘረፉን እንዳዩ ይናገራሉ።

“የአንዱን ቤት እንዳለ ነው የወሰዱትል። የአንደኛውን ስናወጣ በካቢ አካባቢ እንዳለ መጡ። እቃውን ውሰዱ እኛን አትንኩ ብለን እጅ ሰጠን። እኛን መሬት ላይ አስተኝተው አንዳንድ ስልኮችና እዕቃዎች ወሰዱ። እኛ መሬት ላይ ወደቅን፣ ሕይወታችንን አስመለጥን እግዚያብሔር ታድጎናል።” ያሉት ወንጌላዊ ሀብታሙ ፕሪቶሪያ አትረጅቪል ውስጥ እንዲህ ከፍተኛ ዘረፋ ሲፈፀምባቸው የመጀመሪያቸው እንዳልሆነ ይናገራሉ። ከስድት ወር በፊት እንዲሁ የተደራጁ ዘራፊዎች መጥተው ሦስት ሱቆች እንደዘረፏቸው ይገልፃሉ። አሁን የተዘረፈባቸው ከዛ በኋላ መልሰው ያደራጁት ሱቃቸው ነው።

በደቡብ አፍሪካ ንብረታቸውን በዘራፊዎች የተቀሙ ሁለት ኢትዮጵያውያን
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:01 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

“ከዚህ በፊት ሦስት ሱቆች ነበሩኝ ሦስቱም ሲሄዱ እንደገና ከሶማሌዎች ላይ ተበድሬ እቃ አስገባሁበት። አንዱን አቅም ስለሌለኝ ዘጋሁት። ሁለት ነበረኝ ሁለቱም ሄደ እንግዲህ የማይሄድ እግዚያብሔር አለ”

ወንጌላዊ ሀብታሙ የሁለት ልጆቻቸው እና የቤተሰባቸው ቀጣይ ሕይወት ቢያሳስባቸውም እግዚያብሄርን ግን ተስፋ አድርገዋል። “እኔ እንግዲህ እግዚያብሔር በሚያውቀው አቅጣጫ መፀለይ ነው። እግዚያብሔር በሚያውቀው አቅጣጫ ከዚህ ሀገር የሚያስወጣኝ ከሆነም ፀሎት ማድረግ ነው የኔ ሥራ። ቤተሰቦቼን የሰጠኝ እግዚያብሔር እንዲያስበኝ ነው መፀለይ ነው።”ይላሉ።

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሚገኙ እንደ ጆሃንስበርግ፣ ፕሪቶሪያ፣ ደርባ እና ኬፕታውን በመሳሰሉ ዋና ዋና ከተማዎች ውስጥ እንደ ሆቴል፣ ሕንፃ ማከራየት ከመሳሰሉ ትላልቅ የንግድ ሥራዎች ጀምሮ በየመንገዱ ቀበቶ እስከመሸጥ ድረስ ኢትዮጵያውያን በንግድ ሥራ ተሰማርተው ይገኛሉ።ከእነዚህ ሥራዎች ውስጥ ደግሞ እነርሱ “ሎኬሽን” እያሉ በሚጠሯቸው ከዋና ከዋና ከተማ ዋና መንደሮች 20ያና ከዚያ በላይ ኪሎ ሜትር ርቀት ያላቸው “ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ” ያላቸው ሰዎች የሚኖሩበት ሰፈር የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ከፍተው የሚነግዱ ሰዎች ይገኛሉ። እንዲሁም ከመሐል ከተማ አልጋ ልብስና ብርድልብስ እየገዙ በየመንደሩ እየዞሩ የሚሸጡም ይኖራሉ። ወንጌላዊ ሀብታሙ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቃቸው የሚገኘው እንዲህ ባሉ አካባቢዎች እንደሆኑ ሲነግሩኝ “እንዲህ በተደጋጋሚ የሚዘረፉ ከሆነ ለምን እዛ ሄደው ይነግዳሉ?” አልኳቸው።

“እንዴት ልሁን? አሁን ቤተሰቦች አሉኝ የት ልሂድ ታዲያ? አንደኛ ከተማ ውስጥ የቤት ኪራይ ለመክፈል ወደ 30ና 40 ሺህ ፓውንድ ይጠይቃሉ ከየት እናመጣለን። አይገኝም ደግሞ ውድ ነው በጣም ያ አቅም አይኖረንም። “

በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ መጤ የሌላ ሀገር ዜጎች የሀገሬውን ዜጎች የሥራ ዕድል ተጋፍተዋል ፣ የአደንዛዥ ዕፅና ሴተኛ አዳሪነትን አስፋፍተዋል ስለዚህ ሊወጡ ይገባል የሚለው የአንዳንድ የተደራጁ ደቡብ አፍሪካውያን ጥያቄ መነሳት ከጀመረ ረጅም ጊዜን ማስቆጠሩን በዛ ሀገር የሚኖሩ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ከዘጠኝ ዓመት በፊት የ60 ሰዎች የተጨፈጨፉበት እና በርካታ ንብረት የወደመበት አደጋ ተከስቷል። እንዲሁም ከሁለት ዓመት በፊት በሚያዚያ/2007 ዓ.ም እንዲሁ ሰባት ሰዎች በዚህ ምክኒያት ተገለዋል። ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ ኢትዮጵያውያኖች መሆናቸው በወቅቱ ተዘግቧል። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ግን እንደዚህ ካሉት የቡድን ጥቃቶች በተጨማሪም ሁሌም በተናጥል ዘራፊዎች ይጠቃሉ።

መሐመድ አባቦራ የአርብ የካቲት 17/2009 ዓ.ም የመጀመሪያ ጥቃት የተጀመረበት የ“አትረጅቪል” ሰፈር ነጋዴ ነበር። ዝርፊያውን ፈርቶ ዕቃውን ከሁለቱ ሱቆች በመኪና ጭኖ ሊወጣ ሲል ዘራፊዎች ደርሰው እንዳስጣሉት እና ሁሉንም እንደወሰዱበት ይናገራል። ለጊዜው እሱ ጫካ ገብቶ እንዳመለጠ ገልጾ ከሁለት ሱቆች የተረፈው ንብረት እንደሌለ ይናገራል።

መሐመድ ፕሪቶሪያ ከገባ ሰባት ዓመት ሆኖቷል። እስካለፈው ሦስት ዓመት ድረስ በየመንደሩ እየዞረ ብርድልብስና አልጋ ልብስ በመሸጥ ይተዳደር ነበር። ካለፈው ሦስት ዓመት ወዲህ ደግሞ መንደር ውስጥ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ከፍቶ መስራት ጀመረ ነገር ግን ከዘጠኝ ወራት በፊት ሙሉ በሙሉ ዝርፊያ እንደተፈፀመበት ይናገራል። አሁን ደግሞ ገና በሚገባ ሳይጠናከር ሲዘረፍ ሁለተኛው መሆኑ ነው።

ሁለቱም ባለሱቆች መደብሮቻቸው መዘረፉን በከተማው ውስጥ ለሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች አመልክተዋል። ግን ከዚህ ቀደም የመጣ ለውጥ ስለሌለ አሁን የተለየ ነገር እናገኛለን የሚል እምነት የላቸውም።

በፕሪቶሪያ ወርሃዊ መዋጮ የሚከፍሉ 200 ቋሚ አባላት በተጨማሪም ደግሞ ተሳትፎ ብቻ የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን አባላት ያሉት “የሐበሻ ኮሚኒቲ” በሚል መጠሪያ ከአምስት ዓመታት በፊት የተቋቋመው ማኅበር እንዲህ ያሉ በመጤዎች ጥላቻ ላይ የተመሰረተ ጥቃትን ለመከላከል እየሰሩ እንደሆነ ይናገራሉ። በዚህም ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጡ ይናገራሉ ለንግድ ስራ ከሕንድ ላይ የሚከራዩትን ሱቆች ሐበሻ በሌላው ሐበሻ ላይ ከፍተኛ ገንዘብ እየከፈለ ከስራ ማፈናቀል ይደረግበት የነበረውን የቁልፍ ግዢ ማስቀረታቸውን ይናገራሉ። ለመሆኑ ምን ያህል ሱቆች በፕሪቶሪያ ይገኛሉ ስል የማኅበሩን ሰብሳቢ አቶ አለማየሁ ቱጁማን ጠይቄያቸው ነበር። "250 መደበኛ ሱቆችና 200 ተለጣፊ የሚባሉ አሉ" ብለዋል።

አቶ አለማየሁ እንደሚሉት ከሁለት ዓመት በፊት በደርባን እና በጆሃንስበርግ በኢትዮጵያውያን ላይ የደርሰው ጥቃት ከፍተኛ ስለነበር ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ከፖሊስ ጋር ሰርተው ባደረጉት ጠንካራ መተባበር እነዚህን ሱቆች ሊያተርፉ መቻላቸውን ይናገራሉ። እንደ አመጣጣቸው ቢሆን ዋናውን ለስደተኞቹ ፍቃድ ማደሻ መስሪያቤቱን ሲስተም ለመበጣጠስ ሁሉ ሙከራ አድርገው ነበር ብሎናል።

ሌላው የማኅበሩ ጸሐፊ አቶ ሚኪያስ ተሰማ በዚህ ዙር ዝርፊያ የተፈፀመባቸውን አካባቢዎችን ያስረዳል።ሁለቱም የማኅበሩ አባላት እንደሚሉት አሁን ነገሮች ተረጋግተው ወደነበሩበት ተመልሰዋል። በዚህ ዘረፋ ሰኞ ዕለት በተደረገው ዝርፊያ 20 ሱቆች መዘረፋቸውን የሀገሩ መንግስት መግለጹን አርብ ዕለትም እንዲሁ ዝርፊያ መካሄዱን ገልፀው ከዚህ ውስጥ እነርሱ በደረሳቸው ሪፖርት መሰረት የተዘረፉት የሐበሻ ሱቆች አምስት እንደሚደርሱና እያጣሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

በጥቃቱ አንድ የኮንጎ ተወላጅ ከመሞቱና አንድ ከመቁሰሉ ውጭ ምንም አደጋ እንዳልደረሰ ገልፀው። “ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቁት አሰቃቂ ምስሎች ከሁለት ዓመት በፊት የተከሰተውና ከሌላ ሀገር አደጋዎች የተወሰዱ ናቸው” ብለዋል። ከማኅበሩ አመራር አባላት ጋር ፕሪቶሪያ ስለሚገኙ ነጋዴ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን በተመለከተ ያደረኩት ቃለ ምልልስ ሙሉ ክፍል በእሁድ ምሽት ፕሮግራማችን ይቀርባል።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG