በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዓለም የመጀመሪያውን የትሪሊዮን ዶላር ባለፀጋ በአሥር ዓመታት ውስጥ ታያለች


የተስላ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢላን መስክ
የተስላ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢላን መስክ

ዓለም የመጀመሪያውን የትሪሊዮን ዶላር ባለፀጋ “ትሪሊዮኔር” በአሥር ዓመታት ውስጥ ልታይ እንደምትችል፣ ድህነትን በመዋጋት ላይ የሚሠራው ኦክስፋም ኢንተርናሽናል፣ ዛሬ ባወጣውና በዓለም በሚታየው የሃብት አለመመጣጠን ላይ ባተኮረው ሪፖርቱ አመልክቷል።

ሪፖርቱ በዳቮስ፣ ስዊዘርላንድ ከሚደረገው የዓለም የኢኮኖሚ ጉባኤ በተመሳሳይ ወቅት እንዲወጣ የተደረገ ሲሆን፣ በጉባኤው ላይ የሚሳተፉት የፖለቲካ እና የንግድ መሪዎች እጅ እንዲደርስ የታሰበ ነው።

በዓለም የሚታየው የሃብት አለመመጣጠን በየዓመቱ በሚደረገው ጉባኤ ላይ ትኩረት እንዲያገኝ የሚጥረው ኦክስፋም ኢንተርናሽናል፣ አለመመጣጠኑ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ይበልጥ እንደሰፋ አስታውቋል።

የተስላ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚን ኢላን መስክ እና የአማዞኑ መሥራችን ጄፍ ቤዞስን ጨምሮ፣ በዓለም አምስት መሪ ባለፀጋዎች፣ ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ ዓለም በኮሮና ወረርሽኝ ችግር ውስጥ በወደቀበት ወቅት ሃብታቸው 114 በመቶ እንደጨመረ ድርጅቱ ገልጿል።

ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ፣ የመጀመሪያው ቲሪሊዮኔር (አንድ ሺሕ ቢሊዮን ዶላሮች ያሉት ባለ ሃብት) በአሥር ዓመታት ውስጥ ሊፈጠር እንደሚችል ድርጅቱ ተንብይዋል።

ባለ ትሪሊዮን ዶላር ባለቤቱ አሁን በሃብት ማማ ላይ ከወጡት ሰዎች ውስጥ ላይሆንም እናድሚችል የጠቆመው ድርጅቱ፣ እውን የሚሆን ከሆነ፣ ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ አሁን ሳዑዲ አረቢያ ካለት ሃብት እኩል ይኖረዋል ወይም ይኖራታል ማለት ነው ብሏል።

በአሁኑ ወቅት ኢላን መስክ 250 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሃብት ባለቤት በመሆን ቀዳሚውን ሥፍራ እንደሚይዝ የጠቆመው ድርጅቱ፣ በተቃራኒው 5 ቢሊዮን የሚሆኑና በታዳጊ አገራት የሚገኙ ሰዎች ይበልጥ ደሃ ሆነዋል ብሏል። ይህም ባለጸጋ አገራቱ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ቤት በተዋለበት ወቅት ለዜጎቻቸው ሲያደርጉ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ ዓይነት፣ ታዳጊ አገራቱ ማድረግ ባለመቻላቸው እንደሆነ ታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG