ዋሺንግተን ዲሲ —
የዓለም ባንክ ትናንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ “ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ያለባቸው የብድር እዳ ጫና በ12 ከመቶ ጨምሯል፤ እኤአ በ2020 በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት በደረሰው ቀውስ የእዳቸው መጠንም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ 860 ከፍ ብሎ ተመዝግቧል፤ በመሆኑም እዳቸውን መቀንስ የሚያስችል አስቸኳይ ጥረት መደረግ አለበት” ሲል አስጠንቅቋል፡፡
የዓለም ባንክ ድሬክተር ዴቪድ ሜፕላስ፣ የባንኩን የ2022 ዓለም አቀፍ የብድር ስታትስቲክስ ሪፖርት አስመልክቶ፣ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ በዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ላይ ያለው የእዳ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው፡፡ እነዚህን የእዳጫናዎች ለማቃለልም የተቀናጀ ጥረት መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ጂ 20 እና የፓርክ ክለብ አበዳሪ ተቋማት ከፍተኛ የብድር ጫና ያለባቸውን አገሮች እዳ ማቃለል የሚቻልበትን የውዝፍ ብድር እዳ ክለሳና የቅነሳ ማዕቀፍ አስመልከቶ ባለፈው ዓመት ላወጡት መስፈርት፣ እስካሁን ማመልከቻ ያስገቡ አገሮች ኢትዮጵያ፣ ቻድ፣ እና ዛምቢያ ብቻ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡