ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እና የውሃ አቅርቦቷን ለማሻሻል የሚያግዛት የ1 ነጥብ 72 ቢሊየን ዶላር የብድር ስምምነት ከዓለም ባንክ መፈራረሟን የገንዘብ ሚኒስቴር ዛሬ አርብ አስታወቀ።
ከባንኩ ከተገኘው ብድር 523 ሚሊዮን ዶላር የሚደርሰው በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማስፋፋት እና የታዳሽ ኃይል ማመንጫዎችን አቅም ለማጎልበት እንደሚውል የሚኒስቴሩ መግለጫ አመልክቷል።
ተጨማሪ 500 ሚልዮን ዶላር ደግሞ በገጠራማ አካባቢዎች የትራንስፖርት መንገዶችን ግንባታ ጨምሮ የምግብ ገበያ ተደራሽነትን ለማሻሻል ለታቀዱ ሁለት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል መሆኑን መግለጫው ጠቁሟል።
የተፈረው ቀሪው ብድር የውሃ አቅርቦትን ለማሻሽል እና በከተሞች ውስጥ የሥራ ዕድል ላጡ ወጣቶች የሥራ ቅጥር የሚያስገኙ ድጋፍ ሰጪ መርሃ ግብሮች ማሻሻያ እንደሚመደብ ተገልጿል።
ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያጋጠማት ኢትዮጵያ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ጦርነት፣ ድርቅ፣ ጎርፍ እና እንዲሁም በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የአንበጣ ወረርሽኝ ያደረሰው ጉዳት ተደራርበው የተባባሱ ሁኔታዎች መከሰታቸው ተመልክቷል።
በተለምዶ የዓለም ባንክ የሚሰጠው ብድር ከዝቅተኛ ወለድ አንስቶ ከወለድ ነጻ እስከመሆን የሚዘልቅ እና የመክፈያ ጊዜውም ከ30 እስከ 40 ዓመት የሚቆይ ነው።
መድረክ / ፎረም