በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኮቪድ 19 የኤችአይቪን ትኩረት ጎድቶታል


ፎቶ ፋይል
ፎቶ ፋይል

የኮቪድ 19 መግነን ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ ያለ ሰዎች የጤናና ሌሎች አገልግሎቶችን በአግባቡ ማግኘት እንዳይቀጥሉ ያደረገ መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት የኤድስ መቆጣጠሪያ መርኃግብር /ዩኤንኤድስ/ አስታውቋል።

ኮሮናቫይረስ ኤችአይቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተካሄደ ባለው ሥራ ላይ ባሳረፈው ጫና ሰበብ በመጭው የአውሮፓ ዓመት ውስጥ ከ123 ሺህ እስከ 293 ሺህ ሰው ለኤችአይቪ ሊጋለጥ እንደሚችልና ከ69 ሺህ እስከ 148 ሺህ ሰው በኤድስ ምክንያት ሊሞት እንደሚችል መርኃግብሩ ተንብይዋል።

ከኤችአይቪ/ኤድስ ጋር የተያያዙ አድልዎና ማግለልን ጨርሶ በማስወገድ ጉዳይ ላይም አተኩሮ ዛሬ በታሰበው የዓለም ኤድስ ቀን ጥሪ ያወጣው የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋም መንግሥታት ኤችአይቪንና ሌሎችም ዓለምአቀፍ ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚደረጉ ጥረቶች ገፋ ያለ ጥሪት እንዲመድቡና ጥረቶቻቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቋል።

“የተሻሉ ማኅበራዊና የደኅንነት ጥበቃ መረቦች ቢኖሩን ኖሮ ኮሮናቫይረስ እንዲህ ባልተንሠራፋ ነበር” ብሏል ዩኤንኤድስ።

“ሁሉን አቀፍ በሆነ፣ መብቶችን መሠረት ባደረገና ሰዎችን ባማከለ ሁኔታ በቂ ጥሪት ባለማፍሰስና ትኩረት በመንፈግ በኤችአይቪ ምላሽ ላይ ያስከተልነው የጋራ ውድቀት ውድ ዋጋ አስከፍሎናል” ብለዋል የዩኤንኤድስ ዋና ዳይሬክተር ዊኒ ቢያኚማ።

“ለፖለቲካ ሲባል የተሽሞነሞኑ መርኃግብሮች የኮቪድ 19ንም ሆነ የኤችአይቪን ማዕበሎች አያቆሙም” ብለዋል ቢያኚማ በብርቱ ቃላት።

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥም የኤች አይቪ/ኤድስና የኮሮናቫይረስ/ኮቪድ 19ን ጥምር ፈተና ያጎላ የቀጥታ ሥርጭት ፕሮግራም በብሄራው የኤድስ መታሰቢያ ድርጅት አዘጋጅነት እየተካሄደ ሲሆን በዝግጅቱ ላይ የአለርጂና የተላላፊ ደዌዎች ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አንተኒ ፋዉቺና ሌሎችም ባለሙያዎች፣ የአትላንታ፣ የሺካጎና የኒው ዮርክ ከንቲባዎችና ተሟጋቾች እየተሣተፉ ነው።

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ 38 ሚሊየን ሰው ኤችአይቪ በደሙ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ሃያ ስድስት ሚሊየን ሰው ፀረ ኤችአይቪ/ኤድስ መድኃኒቶችን እንደሚጠቀምና ባለፈው 2019 የአውሮፓ ዓመት ውስጥ 690 ሺህ ሰው በኤድስ ምክንያት መሞቱን የዩኤኤድስ መረጃ ይጠቁማል።

XS
SM
MD
LG