በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

 
ኦሮምያ ውስጥ በተቀሰቀሰ ውግያ ብዙ ሰው መገደሉን እማኞች እንደነገሩት አሶሲየትድ ፕረስ ዘገበ

ኦሮምያ ውስጥ በተቀሰቀሰ ውግያ ብዙ ሰው መገደሉን እማኞች እንደነገሩት አሶሲየትድ ፕረስ ዘገበ


ኦሮምያ ክልል ውስጥ በመንግሥት ኃይሎችና መንግሥቱ በሽብርተኛነት በፈረጀው የኦሮሞ ነፃነት ጦር ታጣቂዎች መካከል በተካሄደ ከባድ ውጊያ በአሥሮች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን የዐይን እማኞች እንደነገሩት አሶሲየትድ ፕረስ ከናይሮቢ ዘግቧል። ቡድኑ የሚታገለው ለኦሮሞ ሕዝብ ደኅንነት እንደሆነ እንደሚናገርም ጠቁሟል።

ከኢትዮጵያ ፌዴራል ክልሎች ግዙፏ በሆነችው ኦሮምያ በተለይ በምዕራብ አካባቢዎች ጦርነቱ የተባባሰው በሰሜን ከትግራይ ኃይሎች ጋር የተካሄደውን መጠነ ሰፊ ግጭት ለማስቆም እየተደረጉ ያሉት ጥረቶች በቀጠሉበት ወቅት መሆኑን የዜና ወኪሉ አስታውሷል።

‘ምዕራብ ወለጋ ውስጥ ቢላ በሚባል ከተማ እንደሚኖር የጠቆመ አንድ የዐይን እማኝ ነግሮኛል’ ሲል ኤፒ ባሠራጨው በዚህ ዘገባ “ባለፈው ሣምንት፤ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም በ“ትናንሽ አውሮፕላኖች” ወይም ‘ድሮኖች ሊሆኑ ይችላሉ’ የአየር ላይ ጥቃት ከተካሄደ በኋላ አስከሬኖች በየቦታው ወዳድቀው ማየቱን ገልጿል” ብሏል።

‘በቀል እንዳይደርስበት እንደሚሰጋ ጠቁሞ ማንነቱ እንዳይገለፅ ጠይቋል’ ሲል አሶሲየትድ ፕረስ የሚጠቅሰው ይህ እማኝ "የገበያ ቀን ነበር፤ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት የሚወጡበት ሰዓትም ነበር፤ የሟቾቹን ቁጥር ማስታወስ ባልችልም በአሥሮች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤ ቆስለዋል" ብሏል።

በሰሞኑ ጥቃቶች እማኞች የሚከስሱት በዜና ወኪሉ ዘገባ የትኛውን ማለቱ እንደሆነ በግልፅ ባይሠፍርም “ኢትዮጵያዊያኑ ኃይሎች” ያላቸውን መሆኑን አመልክቷል።

ቢላ ውስጥ ያሉ አንድ ቄስ በድሮን በተፈፀመ ጥቃት ተገድለዋል ያሏቸውን የቤተክርስቲያናቸው አባላት የነበሩ 11 ስዎች አስከሬኖችን መቅበራቸውን ማመልከታቸውንና የቆሰሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም በአቅራቢያ ወዳሉ ሆስፒታሎች መላካቸውን መናገራቸውን ኤፒ ዘግቧል።

ጥቃቱን ተከትሎ ዕሁድ ጠዋት ነቀምት ከተማ ውስጥ በመንግሥቱ ወታደሮችና በአማፂያኑ መካከል ከፍተኛ ውጊያ መደረጉንና ከሰዓት በኋላ የመንግሥቱ ኃይሎች ከተማዩቱን መልሰው መቆጣጠራቸውን እማኝ እንደነገሩት ገልጿል።

የኦሮሞ ነፃነት ጦር ቃል አቀባይ ኦዳ ታርቢ በትዊተር ገፃቸው ባሠፈሩት መልዕክት ታጣቂዎቻቸው ዕሁድ ነቀምት ውስጥ አካሂደዋል ባሉት ዘመቻ “ከ120 በላይ የፖለቲካ እሥረኞችን ለቅቀናል፤ በርካታ የአገዛዙ ወታደራዊ ተቋማት ወድመዋል" ማለታቸውንም የዜና ወኪሉ ጠቅሶ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉ ስለውጊያው ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ እንዳልሰጡትና ሆኖም ግን ‘የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ባለፉት ወራት ጅምላ ግድያ ፈፅሟል’ ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚከስስ አስታውቋል።

ኦሮምያ ውስጥ የተነሳው ግጭት ትግራይ ክልል ውስጥ ከተካሄደው የተለየ ቢሆንም የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትና የትግራይ ኃይሎች የኢትዮጵያን መንግሥት አብረው ለመጣል ጥምረት መፍጠራቸውን ባለፈው ዓመት ይፋ አድርገው እንደነበርም ኤፒ አስታውሷል።

የትግራይን ግጭት በዘላቂነት ለማቆም ባለፈው ሳምንት ስምምነት የተፈረመ ሲሆን ሁለተኛ ዙር የሰላም ውይይት ጎረቤት ኬንያ ውስጥ እየተካሄደ መሆኑንም አሶሲየትድ ፕረስ ጠቁሟል።

XS
SM
MD
LG