የዊኒ ማዲኬዜላ ማንዴላ ሕልፈት አቡነ ዴዝሞንድ ቱቱ ‘ቀስተደመናዪቱ ሃገር’ ሲሉ ከዴሞክራሲያዊው የሥርዓት ለውጥ በኋላ በጠሯት ደቡብ አፍሪካ ለዘመናት የተካሄደውን ፀረ-ዘር መድልዎና ፀረ-ረገጣ ትግሎች ትውስታዎች ከያንቀላፉበት ጥጋጥግ ቀስቅሷል።
ምንም እንኳ የዊኒን የሕይወት ታሪክ የውዝግብና የሁከትም ጥላ ሊያደበዝዘው ሲገዳደረው ቢሰነብትም፤ ዓመታትን ቢያስቆጥርም በዛሬው የመሸኛቸው ሥነ-ሥርዓት ላይ በጎ በጓቸው ሲሞገስ ውሏል። ከሃገሪቱ ልሂቅ እስከ ደቂቅ ያለ ሁሉ መልካሙን ትውስታውን ስለዊኒ ማዲኪዜላ ማንዴላ ከማዝነብ አልሸሸም።
“የዊኒ ማንዴላ ቅርስና የትግሏ ትሩፋት እኮ መንጠፊያ የለውም” ይሉ ነበር የተናገሩ ሁሉ።
ዊኒ ማንዴላ ላባቸውንም፣ ደማቸውንም ሰጥተው ታግለዋል። የዘሮችን እኩልነት በደቡብ አፍሪካ ምድር ላይ ለመደንገግ በጉልህ በሚንፀባረቅ ጀብዱ ታግለዋል። የግል ክፍያ ፈፅመዋል። “የዊኒ ትግል ይቀጥላል” ብለዋል በዚህች ምድር ላይ ሕያው ሰው ሆነው የቆዩባቸውን ዓመታት በክብር ያነሱ፣ የተናገሩ...
የዊኒ አስከሬን የፊታችን ቅዳሜ በመንግሥታዊ የክብር ሥርዓት ወደ ዘለዓለማዊ ማረፊያው ይሸኛል። በዚያ ተገኝተው የዊኒ ማዲኪዜላ ማንዴላን የሕይወት ታሪክ የሚያነብቡት የሃገሪቱ ርዕሰ-ብሄር ሲሪል ራማፖሳ እራሳቸው ናቸው።
ገዥው የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ - ኤኤንሲ ዛሬ መግለጫ አውጥቷል፤ “ዊኒ ማዲኪዜላ ማንዴላ አልሞተችም - አለ - እጅግ በዛች እንጂ!”
የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያንብቡ፤ ቪድዮውን ይመልከቱ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ