በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢላን መስክና የዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ምልልስ


የዓለም ድርጅቱ ዲሬክተር ጄኔራል ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም
የዓለም ድርጅቱ ዲሬክተር ጄኔራል ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

ወደፊት የሚከሰት ወረርሽኝን መከላከል በተመለከተ ሥምምነት ላይ ለመድረስ ድርድር በሚደረግበት በዚህ ወቅት፣ የትዊተር አለቃ ኢላን መስክ ‘አገራት ወረርሽኝን መከላከል በተመለከተ ያላቸውን ሥልጣን ለዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት አሳልፈው መስጠት የለባቸውም’ ብለው ያስተላለፉትን መልዕክት “የውሽት ወሬ” ነው ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ውድቅ አድርጓል።

“ሥምምነቱ የአገራትን ሥልጣን አሳልፎ ለዓለም ጤና ድርጅት ይሰጣል የሚለው ወሬ ውሸት ነው” ሲሉ የድርጅቱ ዲሬክተር ጄኔራል ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መናገራቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

ዶ/ር ቴድሮስ ኢላን መስክን በስም ባይጠቅሱም በትዊተር ባስተላለፉት መልዕክት “አገራት የመወሰን ሥልጣናቸውን ለዓለም ጤና ድርጅት አሳልፈው አይሰጡም” ብለዋል።

“ሥምምነቱ አገራት ወደፊት የሚከሰቱ ወረርሽኞችን በተመለከተ በተሻለ እንዲከላከሉና፣ ሃብታምም ይሁኑ ደሃ አገራት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ከወረርሽኝ ለመክላከለ ሥምምነቱ የተሻለ ሁኔታን ይፈጥራል” ሲሉ አክለዋል ዶ/ ቴድስሮስ።

በዶ/ር ቴድሮስና በኢላን መስክ መካከል የተደረገው ምልልስ የመጣው ወደፊት የሚከሰቱ ወረርሽኞችን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ሥምምነት ለማድረግ አዲስ ረቂቅ በሚዘጋጅበት ወቅት ነው። ሰነዱ በሚቀጥለው ዓመት ግንቦት ድምጽ ይሰጥበታል ተብሏል።

ሥምምነቱ ፈጣን የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር ያስችላል፣ በተጨማሪም በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት በክትባት አቅርቦት ረገድ በባለጸጋና ደሃ አገሮች መካከል የታየው ልዩነት ተመልሶ እንዳይከሰት ይረዳል ተብሏል።

XS
SM
MD
LG