በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"የግጭት አካባቢዎች የጤና ቀውስ አስከትለዋል ተደራሽነትን አግደዋል" - የዓለም ጤና ድርጅት


ፎቶ ፋይል፦ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገ/የሱስ
ፎቶ ፋይል፦ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገ/የሱስ

“ዓለም ለዩክሬን የሰጠውን ያህል ትኩረት ለሌሎቹ አልሰጠም - ነጮች ስላልሆኑ ይሆናል” - ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

የዓለም ጤና ድርጅት፣ የጦርነት ቀጠና በሆኑ የዓለም ክፍሎች የተከሰቱት የተለያዩ ቀውሶች፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የጤንነት ይዞታ እየሸረሸሩ፣ አስፈላጊውን የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትን እንዳይኖር እያገዱ ነው ይላል፡፡

“ጦርነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው ውድመት እና ኮቪድ-19 ዓለማቀፉን ጤና ስጋት ላይ ጥሏል፡፡ በምጣኔ ሀብት የደረጀና የተረጋጋ ማህብረሰ ለመፍጠር የሚያስችለውንም አቅም ጎድቷል” ብሏል፡፡

እነዚህ ዘርፈ ብዙ ቀውሶች ጦርነት ባመሰቃቀቸው ሃገሮች ይበልጥ እየታዩ መሆኑንም አመልክቷል፡፡ ባንድ ወቅት ያበበ ማኅበረሰብ የነበራት ዩክሬን ዛሬ ተዘግታለች፡፡

በሩሲያ ከተወረረችበት የዛሬ 15 ቀን አንስቶ ህፃናትን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ሙትና ቁስለኛ ሆነዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በጤና ባለሙያዎችና ተቋማት ላይ 119 ጥቃቶች መፈጸማቸውን አረጋግጧል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገ/የሱስ በተለይም ውጊያው ዛሬ በተባባሰበት በምስራቅ የአገሪቱ ክፍል የጤና አገልግሎት መስጫዎች ክፉኛ ወድመዋል ይላሉ፡፡

ዳይሬክተሩ ይህን ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፣

“ለሰብአዊነት ሲባል ሩሲያ ወደ ጠረጴዛው ዙሪያ መጥታ ለሰላም እንድትስራ አሳስባለሁ፡፡ ለሰብአዊ የመተላለፊያ በሮች ለመድሃኒት ለምግብና ውሃ አቅርቦት ክፍት መሆን አለባቸው፡፡ ሰላማዊ ሰዎችም ደህንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ መንቀሳቀስ ይችላሉ፡፡”

በሌላ ግንባር የዓለም ምግብ ድርጅት 4.6 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ጦርነት በሚካሄድባት የሰሜን ኢትዮጵያዋ ትግራይ ክልል በከባድ ረሀብ እየተሰቃየ መሆኑንምአስታውቋል፡፡

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ለከፍተኛ የረሃብ አደጋ መዳረጋቸውንም ድርጅቱ አመልክቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የሰብአዊ ተደራሽነት በር መከፈቱን ከሳምንታት በፊት አስታውቋል፡፡

ይሁን እንጂ የዓለም ጤና ድርጅቱ ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

“በታሪክ ረጅሙ የሆነው ከበባ አሁንም ቀጥሏል” ይላሉ፡፡

“ትግራይ እየደረሱ ያሉት የነፍስ አድን አቅርቦቶች እጅግ አነስተኛ መሆኑን”ም ገልጸው ተከታዩን አክለዋል።

“በዚህ የተነሳ የኢትዮጵያና ኤርትራ ኃይሎች ከበባ አሁንም ቀጥሏል፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ለማትረፍና ሰብአዊ አደጋን ለመቀነስ ከበባቸውን ካጠናከሩ ኃያላት ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት ማግኘት ያስፈለገናል፡፡”

ቴድሮስ “ምሰራቅ አፍሪካና ሳህል አካባቢዎች ለከፍተኛ ረሃብ የተጋለጡ ናቸው” ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡

ለዓመታት የዘለቀው ድርቅ፣ ከባድ ጎርፍ፣ እና ኮቪድ-19፣ ሰዎች መሬቶቻቸው የሚያርሱበትን፣ ሰብሎቻቸውን የሚያበቅሉበትና ከብቶቻቸውን የሚያረቡበት አቅማቸውን አውድሟል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

“ብዙ ሰዎች ከወዲሁ ተርበዋል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ካሉበት እየተንቀሳቀሱ ነው”ያሉት ቴድሮስ “ይህ ሰብአዊ ቀውስ በሰዎች ጤንነት ላይና በቀጠናው ደህንነት ላይ የሚያሳድረ ተጽእኖ አሳሳቢ መሆኑን” አስታውቀዋል፡፡

“ዓለም ለዩክሬን የሰጠውን ያህል ትኩረት ለሌሎቹ አልሰጠም - ነጮች ስላልሆኑ ይሆናል” - ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

በሌላም በኩል የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በዩክሬን ጦርነት ላይ ያሳየውን ትኩረት የሳቸው አገር የሆነችው ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች አገሮች አላሳየም” “ይህ እኩል ያልሆነ እይታ እነዚያ እየተሰቃዩ ያሉ ሰዎች ነጮች ስላልሆኑ ሊሆን ይችላል ማለታቸውን አሶሼይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገ/የሱስ ባለፈው ረቡዕ ከጄኔቭ በሰጡት የድረ ገጽ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ “ዓለም በእውነት ለጥቁርና ለነጭ እኩል ትኩረት ቢሰጥ ኖሮ” ብለው የጠየቁት ቴዎድሮስ “በኢትዮጵያ፣ በየመን፣ በአፍጋኒስታን፣ እና በሶሪያ እየተከሰቱ ላሉ አስቸኳይ ቀውሶች የተሰጠው ዓለም አቀፍ ትኩረት ለዩክሬን ከተሰጠው ጋር ሲነጻጸር ቅንጣት ያህል ነው” ብለዋል፡፡

ባላፈው ወር ዶ/ር ቴዎድሮስ በሰጡት መግለጫ “በዓለም ላይ ከትግራይ ውጭ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጤንነት አደጋ ላይ የወደቀበት ቦታ የለም” ብለው ነበር፡፡ ዳይሬክተሩ “አሁን ይህን በምንነጋገርበት ወቅት ብዙ ሰዎች በከፍተኛ ረሀብ እየሞቱ ነው” ብለዋል፡፡

“ይህንን በግልጽና በሀቅ መናገር አለብኝ ዓለም የሰውን ዘር በአንድ ዓይነት መንገድ እያስተናገደች አይደለችም” በማለት ተናግረዋል፡፡

“በትግራይ ያለው ሁኔት እጅግ አሳዛኝ ነው” ያሉት ቴድሮስ “ዓለም ወደ ልቦናው ተመልሶ ሁሉንም የሰውን ልጅ ህይወት እኩል ይመለከታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል፡፡

ፕሬሱ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያሉትን ግፎች በትክክል አለመዘገቡን የተቹት ቴዎድሮስ ሰዎች እስከነ ህይወታቸው የሚቃጠሉበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው “ይህ በሚዲያው በቁምነገር የተወሰደ ነገር ስለመሆኑ እንኳ አላውቅም “ ማለታቸውን አሶሼይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

ጦርነቱንና የሰብአዊ ቀውስን ለተቹት ቴድሮስ ምላሽ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ለዓለም ጤና ድርጅት በላከው ደብዳቤ ቴድሮስን “በስነ ምግባር ጉድለት” ከሷቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በመግለጫው ቴድሮስ ጽ/ቤታቸውን

“ኢትዮጵያን በመጉዳት የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማስፈጸም እየተጠቀሙበት ነው” ሲል ከሷል፡፡

አያይዞም “የህወሓት አባልነታቸውን ቀጥለውበታል” ብሏል፡፡

ቴድሮስ በህወሓት የበላይነት ይመራ በነበረው የአገሪቱ ጥምር የገዥው ፓርቲ ሥልጣን ላይ በነበረ ጊዜ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የጤና ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸውንም የአሶሼይትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG