በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዓለም የጤና ድርጅት የአጣዳፊ ዕርዳታ ክፍል ከባድ የበጀት ችግር ላይ መሆኑ ተገለጠ


ፎቶ ፋይል፦ የዓለም የጤና ድርጅት ጄኔቫ ስዊዘርላንድ እአአ የካቲት 6/2020
ፎቶ ፋይል፦ የዓለም የጤና ድርጅት ጄኔቫ ስዊዘርላንድ እአአ የካቲት 6/2020

የዓለም የጤና ድርጅት አጣዳፊ የጤና ቀውሶች ከመበራከታቸው ተያይዞ በተደቀነበት የገንዘብ ዕጥረት “የህልውና አደጋ” ላይ ደርሷል ሲል በገለልተኛ አካል የተጠናቀረ ሪፖርት አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ ያለበት የገንዘብ ዕጥረት ከባድ ከመሆኑ የተነሳ እአአ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ለሠራተኞች ደመወዝ የሚውል አስችኳይ የገንዘብ ድጋፍ አስፈልጎት እንደነበረ ያመለከተው ሪፖርቱ አሁንም እስከ ቀጣዩ ሰኔ ወር ደመወዝ ለመክፈል የገንዘብ ድጋፍ መጠየቅ ሳይኖርበት እንደማይቀር በዚህ ሳምንት ጄኔቫ ላይ ከሚካሄደው የድርጅቱ ዓመታዊ ጉባዔ አስቀድሞ የወጣው ሪፖርት ጠቁሟል፡፡

የዓለሙ የጤና ተቋም የአጣዳፊ እርዳታ ክፍል እአአ ባለፈው 2023 የሱዳን ጦርነትን ቱርክ እና ሶሪያ ውስጥ የደረሱትን የመሬት ነውጦች፡ የዩክሬይን እና የጋዛ ጦርነት እና ስፋት ያለው የኮሌራ ወረርሽኝ ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ለተከሰቱ 72 አጣዳፊ የጤና አደጋዎች ምላሽ መስጠቱ ተመልክቷል፡፡

ገለልተኛው ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ባወጣው ሪፖርቱ ሀገሮች የራሳቸውን የዝግጁነት ጥረቶች ለማጠናከር መሥራት እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡ የዓለም የጤና ድርጅትም የሚቀርቡለትን የድጋፍ ጥያቄዎች ለመቋቋም ይችል ዘንድ ኃላፊነቶችን ወደ ሀገሮች ባለስልጣናት የሚያዛውርበትን መንገድ ማሻሻል እንዳለበት አመልክቷል፡፡

የዓለሙ የጤና ድርጅት የኣጣዳፊ እርዳታ ክፍል በየጊዜው ለሚነሱ ወረርሺኞች ከሚሰጠው ምላሽ ሌላ ዘላቂ በሆኑ አጣዳፊ የሰብዐዊ ረድዔት ጉዳዮች ውስጥ ስለሚኖረው ሚና አዲስ መመሪያ እንደሚያስፈልገው ሪፖርቱ ሃሳብ አቅርቧል፡፡ አቅማቸው ደከም ያለ በሆኑ ሀገራት የተፈጥሮ አደጋዎች እና ግጭቶች በተበራከቱ ቁጥር በጤና ተቋሙ መርሐ ግብሮች ላይ “የህልውና አደጋ” ሲል የገለጸው አደጋ እንደሚደቀን ሪፖርቱ አስረድቷል፡፡ የሀገሮች ዓቅም የማይጠናከር ከሆነ ድርጅቱ ወሳኝ የሆኑ ሥራዎቹን ለመቀነስ እንደሚገደድ አያይዞ አሳስቧል፡፡

እአአ ባለፈው 2023 ዓመተ ምህረት የዓለም የጤና ድርጅት በንጽጽር የተሟላ በጀት የነበረው ይሁን እንጂ የአጣዳፊ የጤና አደጋዎች መርሀ ግብሮቹ የ411 ሚሊዮን ዶላር ዕጥረት እንደነበረባቸው ያም ከአጠቃላዩ የድርጅቱ በጀት ሢሶ ገደማ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ተቋሙ በጀቱን በሚመለከት የማሻሻያ እርምጃዎች የወሰደ ሲሆን አባል ሀገራቱ በቀረበላቸው ሪፖርት ላይ እንደሚነጋገሩ ታውቋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG