ዋሺንግተን ዲሲ —
አንዳንዶቹ እጅግ የበለጸጉት ሃገሮች ድርጅታቸው ለደሆች ሃገሮች የኮቪድ-19 ክትባት ለማቅረብ የያዘውን ጥረት እያደናቀፉ ናቸው ሲሉ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ድሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ተናገሩ።
ትናንት ዶ/ር ቴድሮስ በጂኔቫ ከጀርመን ፕሬዚዳንት ፍራንክ ዋልተር ስቴይንማየር ጋር ሆነው ለድሆች ሃገሮች ክትባቱን ለማዳረስ በዓለም የጤና ድርጅት አሰባሳቢነት ስለተዋቀረው ኮቫክስ ስለተባለው ስብስብ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
እንዳንዶቹ የበለጸጉ ሃገሮች ኮቫክስ ክትባቶችን ለመግዛት ከተዋዋላቸው የመድሃኒት ኩባኒያዎች ላይ ክትባት ለመግዛት በመዋዋል ኮቫክስ የሚያገኘው ክትባት መጠን እንዲቀንስ እያደረጉ ናቸው ሲሉ ወቅሰዋል። የትኞቹ ሃገሮች እንደሆኑ ግን በስም አልጠቀሱም።
እጅግ ደሆቹ ሃገሮች በቂ ክትባት ማግኘታቸውን ማረጋገጥ ለሁሉም ይበጃል ያሉት ቴድሮስ አድሃኖም ይሄ የበጎ አድራጎት ጉዳይ ሳይሆን የበሽታዎች ሥርጭት እና ቁጥጥር ሳይንሱን መሰረት ያደረገ ግዴታ ነው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሁሉም ጋ ሳይወገድ አንዱ ጋ ብቻ ሊወገድ አይችልም ብለዋል።