በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዓለም የጤና ድርጅት ለአጣዳፊ የጤና አደጋዎች ዕርዳታ ተማጸነ


የዓለም የጤና ድርጅት ለአጣዳፊ የጤና አደጋዎች ዕርዳታ ተማጸነ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:35 0:00

የዓለም የጤና ድርጅት ለአጣዳፊ የጤና አደጋዎች ዕርዳታ ተማጸነ

የዓለም የጤና ድርጅት በ54 ሀገሮች እጅግ አጣዳፊ በሆኑ የጤና አደጋዎች የተጎዱ በሚሊዮኖች የተቆጠሩ ሰዎችን ለመርዳት የሚውል የ2 ነጥብ 54 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ተማጸነ። ገንዘቡ ተደራራቢ በሆኑ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በተከሰቱ አጣዳፊ የጤና አደጋዎች ለተጎዱ መርጃ እንደሚውል አስታውቋል። ድርጅቱ የጠየቀው ገንዘብ እስካሁን ከጠየቃቸው ሁሉ ከፍተኛው መሆኑን ጠቅሳ ሊዛ ሽላይን ለቪኦኤ ከጂኒቫ ዘግባለች፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ተማጽኖውን ሲያቀርቡ ባደረጉት ንግግር "ከዚህ ቀደም ባልታየ ደረጃ ቀውሶች አንድ ላይ ተደራርበው ሲከሰቱ እያየን ነው። ስለሆነም ካሁን ቀደም ከተደረጉት ሁሉ የገዘፈ ምላሽ ይጠይቃል" ብለዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት አንዱ ባንዱ ላይ ተደራራቢ የሆኑ በርካታ የጤና ቀውሶችን እየታገለ መሆኑን አመልክተዋል።

በፓኪስታን የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለውን የጎርፍ አደጋ፥ የሳህል ክልል እና የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ድርቅ እና አጣዳፊ ረሃብ አንስተዋል። እንዲሁም በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት ስለተከተሉ የጤና ችግሮችም አውስተዋል። በኩፍኝ በኮሌራ እና በሌሎችም ገዳይ በሽታዎች ወረርሽኞች እየተጠቁ ያሉ በርካታ ሃገሮች መኖራቸውን አመልክተዋል።

"ዓለም አይቶ እንዳላየ በመሆን እነዚህ ቀውሶች ራሳቸው በራሳቸው መፍትሄ ያበጃሉ ብሎ ተስፋ ማድረግ የለበትም። የገንዘብ ድጋፍ በመስጠት እና ፈጥነን ዕርምጃ በመወሰድ ህይወት ልናተርፍ እንችላለን። ማኅበረሰቦች ከአደጋ እንዲያገግሙ የሚደረጉ ጥረቶችን ልናግዝ እንችላለን። በሽታዎች በሀገር ውስጥ አልፎም ድንበር ተሻገረው እንዳይዛመቱ ለመከላከል እንችላለን። ማኅበረሰቦች ኑሮአቸውን መልሰው ለመገንባት ዕድል እንዲያገኙ እንረዳለን" ብለዋል።

በዓለም ዙሪያ ካሉት ሰብዐዊ ቀውሶች ውስጥ ለሰማኒያ ከመቶው መነሾው ግጭት መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርት ያመለክታል። በዓለም ዙሪያ ከሚደርሰው ለመከላከል የሚቻል የእናቶች እና ህጻናት ሞት ሃምሳ ከመቶው የሚከሰተው በግጭት በተጎዱ እና ለአደጋ በተጋለጡ አካባቢዎች መሆኑን ያስረዳል።

በዓለም ዙሪያ ካሉት የጤና አደጋዎች ከፍተኛውን የተሸከሙት የአፍሪካ ሀገሮች ናቸው።

እአአ ባለፈው 2022 በዓለም ዙሪያ ከተከሰቱት እጅግ አጣዳፊ ተብለው የተፈረጁ የጤና አደጋዎች ውስጥ 64 ከመቶውን የደረሱት አፍሪካ ውስጥ መሆኑን ሪፖርቱ ይጠቁማል።

ፊዮና ብራካ በዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ የአጣዳፊ የጤና አደጋዎች ምላሽ ኃላፊ ናቸው። አፍሪካ በግጭቶች እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተከሰቱ ሰብዓዊ ቀውሶችን እንዲሁም አዳዲስ እና በየጊዜው የሚያገረሹ ወረርሽኞችን ስትታገል መቆየቷን አስገንዝበዋል።

ባለሥልጣኗ ከኮንጎ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ከብራዛቪል በሰጡት ቃል እነዚህን የተወሳሰቡ አጣዳፊ ችግሮች መታገል ቀላል አለመሆኑን አመልክተው ሆኖም የዓለም የጤና ድርጅት እና አጋሮቹ ያደረጉት ድጋፍ በብዙ መንገድ እንደጠቀመ ገልጸዋል።

"ምሳሌ ለመጥቀስ ባሁኑ ጊዜ ሀገሮች የበሽታ ወረርሽኝ ሲቀሰቀስ ከበፊቱ ባጠረ ጊዜ ይደርሱበታል። እንዳይስፋፋም ፈጥነው ይቆጣጠሩታል። ባለፉት ሦስት ዓመታት የኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝን ለመታገል ሥራ ላይ የዋለው መዋዕለ ነዋይ ውጤት እያሳየ ነው። አህጉሪቱ ቫይረሱን የመቋቋም አቅሟ ተሻሽሏል። ለሚከሰቱ አጣዳፊ የጤና አደጋዎች ምላሽ የሚሰጥበት ሥርዓቷም ተጠናክሯል" ሲሉ አስረድተዋል።

ባሁኑ ወቅት የዓለም የጤና ድርጅት በዓለም ዙሪያ ድጋፍ እየሰጠባቸው ያሉ 54 አጣዳፊ የጤና አደጋዎች ያሉ ሲሆን 11ዱ እጅግ ከባድ ወይም 3ኛ ደረጃ ተብለው የተፈረጁ ናቸው። ከነዚህ ሰባቱ አፍሪካ ውስጥ የተከሰቱ የአጣዳፊ የጤና አደጋዎች ሲሆኑ የተቀሩት ዩክሬን፣ የመን፣ አፍጋኒስታን እና ሶሪያ መሆናቸው ተመልክቷል።

XS
SM
MD
LG