በአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች የሚከሰቱ ወረርሽኞች እና ከአየር ንብረት ጋር ተያያዥ የሆኑ አጣዳፊ አደጋዎች ቁጥር በዚህ ምዕት ዓመት ከምንጊዜውም በላይ እየጨመሩ መሆናቸው ተዘገበ። ይህም አስቀድሞም 47 ሚሊዮን ሰው ቸነፈር አፋፍ ላይ ባለበት ቀጣና ውስጥ ያለውን የጤና ቀውስ እያባባሰ መሆኑ ተገልጿል።
የሚበዛው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በብርታቱ በአርባ ዓመታት ውስጥ ባልታየ ድርቅ እየተጠቃ ሲሆን አሁንም ለአምስተኛ ጊዜ መደበኛው ዝናብ አይጥልም የሚል ስጋት እንዳንዣበበ መሆኑ ይሰማል።
በሌላ በኩል ደግሞ በጎርፍ እና በግጭቶች የተጎዱ አካባቢዎችም እንዳሉ ይታወቃል።
የለየለት ቸነፈር ይከሰትባቸዋል የሚል ማስጠንቀቂያ ላይ ካሉት የሶማሊያ አካባቢዎች አንዷባይዶዋ መሆኗን የወደብ ከተማዪቱ የድርቅ ምላሽ አስተባባሪ ጄምስ ኢንዲቲያ አመልክተዋል።
በስፋት በቀጠለው ግጭት ምክንያት ብዙ ሰው ከመኖሪያው መፈናቀሉን የጠቆሙት ኢንዲቲያ ድርቅ በተከሰተ ቁጥር ድኅነቱ እየበረታ እንደሚሄድ ተናግረዋል።