በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኋይት ሐውስ የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ ከሳውዲ አረቢያ ልዑል አልጋ ወራሽ ጋር ተወያዩ


የሳውዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን
የሳውዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን

የኋይት ሐውስ የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ ጄክ ሰለቫን ትናንት ዕሁድ ከሳውዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ጋር ተወያይተዋል፡፡ በውይይታቸው የየመኑን ጦርነት ለማክተም እየተደረጉ ያሉትን ጥረቶች ማንሳታቸውን ኋይት ሐውስ አስታውቋል፡፡

የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ ጄክ ሰለቫን እና የሳውዲው አልጋ ወራሽ መሐመድ ሳልማን ሱዳን ውስጥ እ አ አ ባለፈው ሚያዝያ 15 የተቀሰቀሰውን ውጊያ ተከትሎ ከሀገሪቱ ለወጡት አሜሪካውያን ሳውዲ አረቢያ እያደረገች ስላለው ድጋፍ አንስተው መወያየታቸውን የኋይት ሐውሱ መግለጫ አመልክቷል፡፡

የሳውዲ መንግሥት የዜና ማሰራጫዎች በበኩላቸው በወደብ ከተማዋ ጄዳ ላይ የተካሄደው ውይይት በስትራተጂያዊ ግንኙነቶች ላይ ያተኮረ እንደነበረ ዘግበዋል፡፡

የኋይት ሐውሱ መግለጫ እንዳስታወቀው የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ ጄክ ሰለቫን እና ልዑል ሳልማን ከሁለትዮሽ ውይይታቸው በተጨማሪ ከህንድ እና ከተባበሩት የአረብ ኤሚሬቶች የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪዎች ጋር ሆነው ተወያይተዋል፡፡

ኋይት ሐውስ እንዳለው ውይይቱ መካከለኛው ምስራቅ ጸጥታው በይበልጥ ተጠብቆ እና በልጽጎ ከህንድ እና ከሌላውም የዐለም አካባቢ ጋር የተሳሰረ እንዲሆን ለማስቻል ባላቸው የጋራ ራዕይ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡

የኋይት ሐውሱ የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ እና የሳውዲ አረቢያ ልዑል አልጋ ወራሽ የተወያዩት የሀገሮቻቸው ግንኙነት ውጥረት ላይ ባለበት በዚህ ወቅት መሆኑ ነው፡፡ ለግንኙነቶቻቸው መሻከር ምክንያት ከሆኑት መካከል እ አ አ በ2018 ዐመተ ምሕረት ኢስታንቡል በሚገኘው የሳውዲ ቆንስላ የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ዐምደኛው ጃማል ካሽሾጊ ላይ የተፈጸመው ግድያ እና በሳውዲ የሚመራው የነዳጅ አምራች ሀገሮች ማህበር “ኦፔክ” የነዳጅ ምርቱን መቀነሱ ይገኙበታል፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ የደህንነት ተቋማት ግምገማ መሰረት ጃማል ካሽሾጊ ተይዞ የተገደለው በሳውዲው አልጋ ወራሽ ይሁንታ ነው፡፡ ሳውዲ አረቢያ ታስተባብላለች፡፡

XS
SM
MD
LG