በሰሜን ኢትዮጵያ በግጭቱ መባባስ የዓለም ምግብ ድርጅት ተሽከርካሪዎች ካለፈው ታህሳስ ወር አጋማሽ ጀምሮ መቀሌ መድረስ ያልቻሉ መሆኑን ድርጅቱ በመግለጫ አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ትላንት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት ለትግራይ ክልል ህዝብ የዕለት ደራሽ እርዳታ ያለ ምንም መስተጓጎል እንዲቀርብ ለማስቻል በየጊዜው ከአጋር አካላት ጋር ምክክር በማድረግ እየሠራ ይገኛል ብሏል፡፡
የምግብ ድርጅቱ በትግራይ 2.1 ሚሊዮን በአማራ 650ሺ እንዲሁም በአፋር 534ሺ ሰዎች ዘንድ የምግብ እርዳታ ለማድረስ ያቀደ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ በገንዘብ እጥረት ሳቢያ በሚቀጥለው ወር በሁሉም የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች የምግብና እርዳታ ሊኖረው እንደማይችል አስታውቋል፡፡ በመሆኑም የ337 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ እርዳታ የጠየቀ ሲሆን በሶማሊያ ድርቅ ለተጎዱ 170 ሚሊዮን ጠይቋል፡፡
የዓለም ምግብ ድርጅት በበኩሉ ሁሉም ወገኖች ግጭቱን አቁመው የእርዳታውን አቅርቦት መስመር ክፍት እንዲያደርጉ በዛሬው መግለጫው ጠይቋል፡፡