በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዓለም የምግብ ፕሮግራም መግለጫ


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም በርካታ ችግሮች ያሉ ቢሆንም ባለፉት እአአ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ በሰሜን ምዕራብ እና በከፊልም በደቡባዊ ትግራይ ለአንድ ሚሊዮን ነዋሪዎች የምግብ እርዳታ ልናደርስ ችለናል ሲል አስታወቀ፡፡

ሆኖም ባለው የምግብ የገንዘብ እና የቴሌኮሙኒኬሽን መገናኛዎች ዕጥረት የተነሳ ልንደርስ የቻልነው የረሃብ ቸነፈር አፋፍ ላይ ያሉትን ጨምሮ በዕቅዳችን ከያዝናቸው ሰዎች ውስጥ ግማሹን ብቻ ነው ሲል አስታውቋል፡፡

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከዚህ ነሃሴ ወር ጀምሮ ለሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሰዎች አጣዳፊ የምግብ እርዳታ ለማቅረብ ዕቅድ ያለው መሆኑን ገልጾ ይህን ዕቅዱን ለማሳካት በየሳምንቱ ቢያንስ ስድስት ሽህ ሜትሪክ ቶን ምግብ እንደሚያስፈልገው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በቅርብ ሳምንታት በጸጥታው መደፍረስ እና በእንቅስቃሴ ገደቦች የተነሳ ባቀድነው መጠን የምግብ እርዳታውን ወደክልሉ ለማስገባት አልቻልንም ብሏል፡፡

በፈረንጆች ነሃሴ የመጀመሪያ ሳምንት ውስጥ በአባላ መተላለፊያ በኩል ከ175 በላይ እርዳታ የጫኑ መኪናዎች ትግራይ መድረሳቸውን ገልጾ ከዚያም ውስጥ ዘጠናው ከ5000 ቶን በላይ ህይወት አድን የምግብ እርዳታ የጫኑ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡

በቀጣዮቹ ቀናት ደግሞ ተጨማሪ ምግብ፣ ነዳጅ፣ አልሚ ምግቦች እንዲሁም የጤና የንጽህና እና የመጠለያ ቁሳቁስ የጫኑ መኪናዎች ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የመንግሥታቱ ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ገልጿል፡፡

ባለፈው ወር ውስጥ ትግራይ ውስጥ በሰባአዊ እርዳታ ዕጥረት ምክንያት ሰዎች ለስቃይ ተዳርገዋል፣ አሁንም ለረሃብ ቸነፈር ከመጋለጣቸው በፊት ሊደረስላቸው ይገባል ያሉት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የትግራይ ምላሽ ክፍል ዳይሬክተሩ ማይክል ደንፎርድ ሁሉም ወገኖች ተኩስ በማቆም ነፍስ አድን የሰብዐዊ ረድዔት ባልተገደበ መንገድ ሳይዘገይ እንዲደርስ ዋስትና እንዲሰጡ እንጠይቃለን ብለዋል፡፡ አስከትለውም በአጎራባች የአማራ እና የአፋር ክልሎችም በግጭቱ ምክንያት ነዋሪዎች ይበልጡን ወደረሃብ አደጋ እያመሩ መሆኑን ገልጸው ድርጅታቸው ችግር ላይ ላሉት ማኅበረሰቦች ባፋጣኝ ህይወት አድን የምግብ እርዳታ ለማድረስ ስለሚቻልበት መንገድ ከመንግሥቱ ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

XS
SM
MD
LG