በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ አሠራር ሊጀምር ነው


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም (ዳብልዩ.ኤፍ.ፒ.) ኢትዮጵያ ውስጥ አቋርጦት የነበረውን የምግብ እደላ በተሻሻለ አሠራር ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።

እርዳታው ‘እየተሰረቀ ከታለመበት ዓላማ ውጭ ይውላል' በሚል ካለፈው ሰኔ አንስቶ ተቋርጦበት የቆየውን 3 ሚሊየን 2 መቶ ሺህ ተረጂ መድረስ የሚያስችል እርምጃ እንደሆነ ድርጅቱ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መርኃግብሩን ለመጀመር የወሰነው ግልፅ፣ በማስረጃ የተደገፈና በገለልተኛ አሠራር ላይ ያተኮረ የተሟላ ግምገማውን ካጠናቀቀ በኋላ መሆኑን ዳብልዩ.ኤፍ.ፒ. ጨምሮ ገልጧል።

አዲሱ አካሄድ “በስፋት የተሞከረና ጠንካራ የቁጥጥር አሠራር የተከተለ ይሆናል” ሲል ድርጅቱ ዛሬ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክቷል።

እርዳታው በእጅጉ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖችና የቤተሰቦቻቸውን አባላት ግልፅ በሆነ መመዘኛ ለመለየት ከያካባቢው ማኅበረሰቦች ጋር በቅርበት መሥራት፤ ምግብ ከሚከማችባቸው መጋዘኖች እደላው ወደሚካሄድባቸው አካባቢዎች በሚጓጓዝበት ወቅት የተጠናከረ ክትትል እንደሚደረግም መግለጫው ይዘረዝራል።

በተጨማሪም የምግብ ዕርዳታ ከታለመለት ዓላማ ውጭ እንዳይውል ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግና ውሎ በሚገኝበትም ወቅት በፍጥነት ሪፖርት ማቅረብ የሚያስችሉ ዘዴዎችን ተግባራዊ እንደሚያደርግ መግለጫው አስረድቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG