በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የድርቅና የረሃብ ሁኔታ በደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ


በዚህ ዓመት አጠቃላዩ ተረጂ 4 ነጥብ 3 ሚሊየን ሰው መሆኑን የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ በደቡብና በደቡብ ምሥራቅ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ ሣቢያ የተረጂው ቁጥር 2 ነጥብ 8 ሚሊየን መሆኑን፤ በመላ ሃገሪቱ የምግብ እርዳታ ፈላጊው 3 ነጥብ 2 ሚሊየን እንደሚደርስና የዓለም የምግብ ፕሮግራም የያዛቸውን ተደራቢ የድጋፍ አቅርቦቶችን ጨምሮ በዚህ ዓመት አጠቃላዩ ተረጂ 4 ነጥብ 3 ሚሊየን መሆኑን የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስታውቋል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ወደ ስምንት ሚሊየን የሚሆን ሕዝብ አጣዳፊ የምግብ እርዳታ ፈላጊ ነው፡፡ ፅ/ቤታቸው ናይሮቢ-ኬንያ የሚገኘው የዓለም የምግብ ፕሮግራም የአፍሪካ አካባቢ ቃልአቀባይ ሚስተር ፒተር ስሚርዶን እንደሚሉት የዘንድሮው ሁኔታ (በአ.ዘ.አ) ከ2007 እስከ 2009 ዓ.ም ከነበረው የከፋ ሁኔታ የተለየና የረገበ ነው፡፡

በእነዚያ ዓመታት፣ በተለይ በ2009 ዓ.ም መጀመሪያ የደረሰው ድርቅ ለሃያ ሚሊየን ሰው መራብ ምክንያት ሆኖ እንደነበር ሚስተር ስሚርዶን አስታውሰዋል፡፡

የዘንድሮው ድርቅ መንስዔ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆየው የክረምት ዝናብ አንድም አነስተኛ መሆኑ፣ አልያም አሁንም በድርቅ በተጠቁት አካባቢዎች ከመደበኛው በታች መሆኑን የገለፁት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ በዘንድሮው ድርቅ የተጠቁት አካባቢዎች ፈጥነው ያገግማሉ ብለው እንደማይጠብቁና ከዚህም ጋር ተያይዞ ሰብዓዊ እርዳታና የምግብ አቅርቦት የሚፈልገው ሰው ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አሳስበዋል፡፡

በመጭው ሐምሌ ቅኝትና ፍተሻ እንደሚያደርጉ ሚስተር ስሚርዶን ገልፀው አሁን በእጃቸው ባለ መረጃ መሠረት ከስምንት ሚሊየኑ የአፍሪካ ቀንድ ምግብ ፈላጊ ስድስት ሚሊየኑ የእርሣቸውን ተቋም እጅ እንደሚጠብቅና ከዚያ ውስጥ ደግሞ ከሁለት ሦስተኛ በላይ የሚሆነው በኢትዮጵያ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ለዝርዝሩና ለተጨማሪ መረጃ ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG