የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት እየተባባሰ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ዩናይትድ ስቴትስ በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን ወታደራዊ ዝግጁነት ማጠናከሯን፣ ትላንት እሑድ በአጽንዖት አስታውቃለች።
የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት እየተባባሰ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን ወታደራዊ ይዞታ እንዳጠናከረች፣ ትላንት እሑድ፣ በአጽንዖት ያስታወቀችው ዩናይትድ ስቴትስ፣ ለማናቸውም ደራሽ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ እንደምትሰጥም አስጠንቅቃለች።
የእስራኤል ወታደሮች፣ ከታጣቂው የፍልስጥኤም ቡድን ሐማስ ጋራ ለሚያካሒዱት ቀጣዩ ጦርነት እየተዘጋጁ ሲኾን፣ ግጭቱ የበለጠ ሊስፋፋ ይችላል፤ የሚለው ስጋት አልቀነስም።
በዚኽ ኹኔታ ውስጥ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ተጨማሪ የአየር መከላከያ መሣሪያዎችን ወደ ቀጣናው እንዳሰማራች አስታውቃለች።
የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን፣ ይህንኑ ርምጃ አስመልክቶ፣ “በዚኽ ሳምንት” በተሰኘው የኤቢሲ ቴሊቪዥን ፕሮግራም ላይ፣ በቅርብ ጊዜ፣ የአገሪቱ ጦር በሚገኝባቸው በኢራቅ እና በሶሪያ ባሉ ወታደራዊ መደቦች ላይ የተሰነዘሩ የሮኬት እና የዩኤቪ ጥቃቶችን እንደተመለከቱ አውስተዋል፡፡ አያይዘውም፣ “ራሳችንን የመከላከል መብታችንን እናስጠብቃለን፤ ተገቢውን ርምጃ ከመውሰድም ወደ ኋላ አንልም፤” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
በቅርቡ ክልሉን የጎበኙት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከንም፣ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር፣ በስፍራው ይዞታውን የማጠናከር ርምጃ አይቀሬ እንደኾነ አረጋግጠዋል፡፡
ብሊንከን በኤንቢሲ ቴሌቪዥን፣ “ሚት ዘፕሬስ” በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ “ሁለተኛ ወይም ሦስተኛ ግንባር ተፈጥሮ ማየት አንፈልግም። ኃይሎቻችን ወይም ወታደሮቻችን ጥቃት ሲሰነዘርባቸው ማየት አንፈልግም፡፡ ያ ኾኖ እና ደርሶ ከተገኘ፣ ለዚያ ዝግጁ ነን፤” ብለዋል፡፡
በእስራኤል እና ሐማስ ግጭት በተስጓጎለው የጋዛ ሰብአዊ አቅርቦት በኩል፣ ቱርክ ለፍልስጥኤም ሲቪሎች ርዳታ ከሚልኩ የቅርብ ጊዜ አገሮች አንዷ ኾናለች።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዲሬክተር ሲንዲ መኬይን፣ ከኤቢሲ ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በግብጽ - ራፋህ በኩል ወደ ጋዛ አቋርጠው የሚገቡ፣ ምግብ እና መድኃኒት የጫኑ ተሽከርካሪዎች ፍሰት፣ በጣም አዝጋሚ እንደኾነ ተናግረዋል።
“ትላንት ምሽት፣ ወደ 200ሺሕ የሚጠጉ ሰዎችን ራት ብንመግብም፣ የጠብታ ያህል እንጂ በቂ አይደለም፤” ያሉት መኬይን፣ “ሰዎች እየተራቡ ነው፡፡ ይህም ደግሞ በክልሉ ውስጥ ላሉ ሁሉ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ ነው፤” ሲሉ አሳሳቢነቱን አመልክተዋል፡፡
ይህንኑ የመካከለኛው ምሥራቅ አስጊ ኹኔታ የሚጋሩት፣ የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሪፐብሊካኑ ማይክል ማኩል፣ በዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አብላጫው መቀመጫ የያዙት ሪፐብሊካኖች፣ “አፈ ጉባኤቸውን መምረጣቸው አስፈላጊ ነው፤” ሲሉ መክረዋል፡፡
በኤቢሲ ቴሌቪዥን የቀረቡት ማኩል፣ አፈ ጉባኤ ኬቨን ማካርቲ፣ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ከሥልጣን ከተባረሩበት ጊዜ ጀምሮ፣ ባዶውን የቀረውን ወንበር የመሙላትን አስፈላጊነት ተናግረዋል፡፡
“ዓለም በእሳት ላይ ናት። ይህ እኛ እያደረግን ያለነውም በጣም አደገኛ ነው፤” ያሉት ማኩል፣ “ከሁሉም በላይ ደግሞ አሳፋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ጠላቶቻችንን፣ ዐቅም እንዲኖራቸው የሚያደርግና የሚያበረታታ ነው፤” ብለዋል፡፡
ጉዳዩ፣ እጅግ አስቸኳይ እና አሳሳቢ ቢኾንም፣ በዚኽ ሳምንት አፈ ጉባኤ ይመረጥ እንደኾነ ወይም ሒደቱ እንዴት እንደሚካሔድ እንደማያውቁ፣ ማኩል ሳይናገሩ አላለፉም፡፡
መድረክ / ፎረም