ከዋግ ኽምራ ብኄረሰብ አስተዳዳር ዞን አካባቢዎች ተፈናቅለው ከሰቆጣ 30 ኪሊ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው “ወለህ” መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ “ኽምጠኛ” ተነጋሪ ተፈናቃዮች ትምሕርታቸውን በድንኳን ውስጥ በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ገለፁ።
በዞኑ ትምሕርት መምሪያ የተፈናቃይ ተማሪዎችን ጉዳይ የሚከታተለው ዘርፍ አስተባባሪ ብርሃኑ ፋንታዬ ትምሕርቱ እየተሰጠ የሚገኘው በሦስት መጠለያ ጣቢያዎች መሆኑን ገልፀው ከሦስት ሺሕ በላይ ተፈናቃይ ተማሪዎች በድንኳንና በዛፍ ጥላ ስር ትምሀርታቸውን እንዲከታተሉ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ይሁን እንጅ ለመማር ማስተማሩ የሚያስፈልጉ ግብአቶች ባለመሟላታቸው ተማሪዎች ብቁ ለማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን ገልፀዋል።
ተፈናቃይ ተማሪዎችና መምህራን ትምሕርት መጀመሩን በበጎ ቢያዩትም የምግብ፣ የአልባሳትና የመማሪያ ድንኳኖች እጥረት እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡
በበርሃማ አካባቢ እጅግ ሞቃታማ በሆነ የዓየር ንብረት በአንድ ድንኳን ውስጥ ከመቶ በላይተማሪዎች ተጨናንቀው እንደሚማሩ ቪኦኤ ያናገራቸው አስተያየት ሰጭዎች ተናግረዋል፡፡
ከአበርገሌ፣ ጻግብዥና ከፊል ሰቆጣ አካባቢ የተፈናቀሉ ሰዎች ባረፉበት ወለህ መጠለያ ጣቢያ 1448 ተማሪዎች መደበኛ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ በመጠለያ ጣቢያው እንደ መማሪያ ክፍል የሚያገለግሉት ከዩኒሴፍ ተገኙ የተባሉ ድንኳኖች ናቸው፡፡
ኽምጠኛ ተነጋሪው አረጋይ ኃይሌ ከአበርገሌ በጦርነቱ ምክንያት ወደ ሰቆጣ ከዚያም ከሰቆጣ ከተማ 30 ኪ.ሜ ርቀት በሚገኘው በወለህ መጠለያ ካምፕ የስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን በመማር ላይ ካሉት ተፈናቃዮች አንዱ መሆኑን በስልክ በአስተርጓሚ ገልጾልናል።
የወላጆቹን ደኅንነት አለማወቁ ትምሕርቱን በተረጋጋ መንፈስ ለመከታተል እንቅፋት እንደፈጠረበትም ይናገራል፡፡
ሲፈናቀል ለብሶት ከመጣው አልባሳት፣ ቀናት ተቆጥረው ከሚሰፈርለት ዱቄትና አልፎ አልፎ በት/ቤት ከሚሰጠው ብስኩት በቀር የምግብ እጥረት እንዳለባቸው ጠቁሞ በጎ አድራጊዎች የተራድኦ እጃቸውን እንዲሰነዝሩ ጠይቋል፡፡
ከዩኒሴፍ በተገኘው ድንኳን ውስጥ ወለል ላይ ተቀምጠው ትምህርታቸውን ለመከታተል ቢሞክሩም ከአካባቢው በርሃማነት ጋር ተያይዞ በአንድ ድንኳን እስከ መቶ ተማሪዎች ተጨናንቀው ስለሚማሩ ለተላላፊና ለሌሎች የጤና ችግር እንዳይጋለጡ ሥጋት መኖሩን ከአካባቢዎቹ የሚወጡት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
አንዳንዶችም ጥላ ስርና ዳስ ጥለው የሚማሩ መኖራቸውን የተፈናቃይ ተማሪዎች ጉዳይ አስተባባሪው አመልክተዋል፡፡
ተፈናቃይ ተማሪዎችና መምህራን ባሉበት እንዲታገዙና የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል ከተደረገ ሁለት ወራት ማለፋቸውን የሚገልጹት አስተባባሪው በተለይ ህጻናት ተማሪዎችን ወደ ትምህርታቸው በመመለስ ከደረሰባቸው የሥነ ልቦና ጭንቀት ለማውጣት የተጀመረው ጥረት አንጻራዊ ስኬት እንዳለው ይናገራሉ።
ይሁን እንጅ እንደ አስተባባሪው አምና ትምህርታቸውን ይከታተሉ ከበሩት ውስጥ ዘንድሮ መቀጠል የቻሉት 17 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡
ትምህርቱን ለማስቀጠል መሞከሩ አበረታች ጅምር ቢሆንም ለተማሪዎቹና ለትምህርት ባለሙያዎቹ የሚያስፈልጉ ግብአቶች አለመሟላታቸው እንቅስቃሴው ላይ ተጽእኖ ማሳረፉን ዘርዝረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የግል ንጽህና መጠበቂያ ግብአቶች፣ የአልባሳትና መሰል ቁሳቁሶች እጥረት መከሰቱን አክለው አብራርተዋል፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።