የትግራይ ክልልን መነሻ አድርጎ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የመከራ ወራት፣ ከሥራቸው በመስተጓጎላቸው እና ደመወዛቸውም በመቋረጡ፣ ለረኀብ እና ለጤና እክል የተጋለጡ ሠራተኞችን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚገኙበትን አስቸጋሪ ኹኔታ በልዩ ልዩ ዘገባዎቻችን ስናስቃኝ ቆይተናል፡፡
ከእነርሱም መካከል፣ የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ፣ ባለፈው መጋቢት ወር፣ የአሜሪካ ድምፅ እንግዳ የነበረችው፣ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ መምህርት ብርሃን ወልደ ገብርኤል አንዷ ናት፡፡
የጦርነቱን አስቸጋሪ ወራት፣ በመቐለ ከተማ ጎዳናዎች ጋሪ እየገፋች፣ ለቤት ፍጆታ የሚውሉ አስቤዛዎችን እየሸጠች ሕይወቷን ለማቆየት የተገደደችው የዩኒቨርሲቲ መምህርቷ ብርሃን ወልደ ገብርኤል፣ የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ወደ ሥራዋ ተመልሳለች፡፡
መምህርቷ ወደ ሥራዋ ከተመለሰች በኋላ፣ ለሁለት ዓመት የቆየችበትን የጎዳና ላይ ንግድ ብታቋርጥም፣ በተደረግላት የተወሰነ ድጋፍ የከፈተችውን አነስተኛ ሱቅ፣ አሁንም እየሠራችበት ትገኛለች፡፡
ይህንና ዛሬ ያለችበትን አጠቃላይ የኑሮ ኹኔታ ለማስቃኘት፣ ወደ አክሱም ከተማ ተጉዘን አነጋግረናታል፡፡
መድረክ / ፎረም