በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የአዙሳ ዩኒቨርሲቲ የክብር ስነ-ስርዓት መሰረዝና ያስከተለው ውዝግብ


ቪኦኤ
ቪኦኤ
please wait

No media source currently available

0:00 0:24:14 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ


ነሐሴ 6 2006ዓም የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የአማርኛዉ ቋንቋ አገልግሎት በኢትዮጵያ መንግሥትና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን (ዳያስፖራ) መካከል ያለዉን ግንኙነት የገመገመ ዝግጅት ማቅረቡ ይታወሳል።

በዝግጅቱ ዉስጥ ከተካተቱት በርካታ ርእሶች መካከል የካሊፎርኒያው አዙሳ ፓሲፊክ ዩኒቨርሲቲ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ሊሰጥ አቅዶ የነበረዉ የክብር ስነስርዓት የሰረዘበት ምክንያት አንዱ ነበር። ርዕሰ ጉዳዩን አስመልክቶ የተጠናከረ ዘገባ በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ መሰራጨቱን ተከትሎ፤ አንዳንድ የአሜሪካ ድምጽ ጋዜጠኞች “ሆን ብለዉ እዉነትን አዛብተዋል።” የኢትዮጵያ ሕዝብ “የዳያስፖራዉን ድምጽ እንዳይሰማ አፍነዋል” የሚሉና በተለይም አዙሳ ዩኒቬርሲቲ ሽልማቱን እንዲሰርዝ ዘመቻ ካደረጉት አንዱ ጋዜጠኛና የፖለቲካ አክቲቪስት አቶ አበበ ገላዉ ቪኦኤ ላይ ያቀረባቸዉ ክሶች በራሱ ድረ ገጽ አዲስ ድምጽ፣ በኢሳትና በሌሎች የዳይስፓራ መገናኛ ብዙሃን ሲሰራጭ ሰንብቷል።

ከአቶ አበበ ገላዉና የዋሽንግተን ዲሲ ኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጣምራ ግብረ-ሃይል ከተባለው የዳያስፖራ ቡድን ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ አስተዳደር የተቃዉሞ ደብዳቤዎች ደርሰዋል። የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮም በዝግጅቶቹ ላይ ከማንኛውም ወገን የሚቀርቡ ተቃውሞዎችንና ትችቶችን ትኩረት ሰጥቶ ያጣራል። በዚህም መሰረት የጣቢያው ሃላፊዎች የፕሮግራሞችን ይዘት የሚገመግም ገለልተኛ አጣሪ ቡድን መድበው፤ የፕሮግራሙን ይዘት አስመርምረዉ ለአቶ አበበ ገላዉ ኦፊሴል ምላሽ ሰጥተዋል።

ቀጥለን በምናቀርበዉ ዝግጅት የነሐሴ 6ቱን ዘገባ ዋና ዓላማና የተጠናቀረበትን ሁኔታ፣ የገለልተኛውን አጣሪ ቢሮ ድምዳሜዎች፣ እንዲሁም ከፕሮግራሙ ሰፊ ክፍል በአንድ ነጥብ ላይ የተፈጠረዉን ዉዥንብር ግልጽ ካደረግን በኋላ፤ አሻሚ የሆኑና የተሳሳትንባቸው ነጥቦች ላይ ማስተካከያ ለመስጠት ነው።

የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ገለልተኛ አጣሪ ቡድን፤ የነሐሴ 6ቱን ዝግጅት ወደ እንግሊዝኛ አስተርጉሞ ይዘቱን እስኪያጣራ ጊዜ ስለወሰደ በፕሮግራም ላይ ማብራሪያ ለመስጠት መዘግየቱን እናምናለን። ለዚህም አድማጮቻችንን ይቅርታ እንጠይቃለን።

ነሐሴ 6 2006 ዓ.ም. በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የአማርኛዉ ቋንቋ የተሰራጨዉ ዘገባ የኢትዮጵያን መንግስትና በዉጪ አገሮች በተለይም በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ የሚኖረዉን የትዉልደ ኢትዮጵያ ማህበረሰብ ግንኙነት የገመገመ ነበር። በዋሽንግተንና አካባቢዋ የኢትዮጵያን መንግስት ፖሊስ የሚነቅፉና የሚደግፉ እንዳሉ ሲታወቅ፤ በሀምሌ ወር መጨረሻ ላይ በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደዉ የUS እና የአፍሪቃ መሪዎች ጉባኤ ላይ የተገኙ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ከዳያስፖራዉ የገጠማቸዉ ተቃዉሞ ትኩረት የሚስብ ነበር።

የመሪዎቹ ጉባኤ በተከፈተበት ሰኞ ሃምሌ 28 ቀን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ ትዉልደ ኢትዮጵያ የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ ነዋሪዎች የኢትዮጵያ መንግስትን ፖሊሲና የስብአዊ መብት አያያዝ በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል። የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ በዚያ ተቃዉሞ ሰልፍ ላይ ያጠናቀረዉን ዘገባ በወቅቱ አስራጭቷል።

ጉባኤዉን ለመካፈል ዋሽንግተን የተገኙ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከዳያስፓራ አክቲቪስት ወይም የፖለቲካ ለውጥ አራማጆች በተናጠል የገጠማቸዉ ተቃዉሞ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንና Youtube ተሰራጭቷል። የኢትዮጽያ መንግስት ኮሚኒኬሽንስ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን በአንድ የቨርጂኒያ የልብስ መደብር ዉስጥ እንዲሁም የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ላሊበላ በሚባል የዋሽንግተን ዲስ ምግብ ቤት ዉስጥ ከዳያስፖራ የፖለቲካ ለውጥ አራማጆች የገጠማቸዉ ተቃዉሞ በምሳሌነት ይጠቀሳል። እነዚህ ክስቶች ዜና ከመሆናቸዉም በላይ፤ የኢትዮጵያ መንግስትን ከሚተቸዉ ዳያስፖራ ተቃዉሞው እየሰላ መምጣቱን የሚያሳዩ ናቸዉ።

በሌላ በኩል በዘገባው እንደቀረበው የኢትዮጵያ መንግስት በሚቆጣጠራቸዉ መገናኛ ብዙሃን በዳያስፖራዉ ኑሮ አሉታዊ ፕሮግራሞች ያቀርባሉ። በኢትዮጵያ ቴሌቪዢን የሚቀርቡ የድራማ ዝግጅቶት በዉጭ አገር ተምረዉ ኑሯቸዉን አሸንፈዉና ለማህበረሰቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት ኢትዮጵያዊያን ኑሮ ይልቅ ሳይሳካላቸው የቀሩና ቤት አልባ የሆኑ ምሳሌዎች ላይ በማትኮር የስላቅ ትረካ ከሚቀርብባቸው ድራማዎች ከአንድ ሙዚቃው ጋር ቀንጭቦ አቅርቧል።

ዘገባው ሲቀጥል በዉጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዉን ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት የኢኮኖሚ ምንጭ መሆናቸውን ያትታል። በሰዉ እጅ በአደራ ለዘመድ ወዳጅና ለልዩ ልዩ ወጪዎች ድጎማ ወደ አገር የሚገባዉ ገንዘብ ሳይሰላ በኦፊሴል በባንክ ከዳያስፖራ የሚላከዉ ገንዘብ ለአገሪቱ የዉጪ ምንዛሪ ከሚያሰገኙ ምርቶች ገቢ የላቀ መሆኑን ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ይናገራሉ። በዓመት ከዳያስፖራ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባዉ የገንዘብ መጠን ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን የዓለም ባንክ መረጃ ይናገራል።

የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ዘገባ ታዲያ እነዚህን ጭብጦች የዘረዘረና በዳያስፖራና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ያለዉ ልዩነት መካረር ለምን? እንዴትስ ቢሆን ይፈታል? የሚል ግምገማ ያቀረበ ነዉ። እነዚህን ነጥቦች የገመገሙልን በየጊዜዉ ሚዛናዊ ትንታኔ ወይም አስተያየት የሚሰጡን የሕግ ባለሙያ አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ ናቸዉ። ስለዳያስፖራ ተቃዋሚዎችም ሆነ ስለኢትዮጵያ መንግስት የሰጡን ግምገማ ከነሙሉ ዘገባው በድረ-ገጻችን www.voanews.com ላይ ይገኛል።

አስራ አንድ ደቂቃ ርዝመት ያለው የነሐሴ 6ቱ ዝግጅታችን አብላጫው ክፍል በነዚህ ርእሶች ላይ ያተኮረ ነው። በካሊፎርኒያ የሚገኘዉ የአዙሳ ፓሲፊክ ዩኒቨርሲቲ፤ ከዚያ ዲግሪያቸዉን ላገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም የክብር ስነስርዓት ለማድረግ የነበረዉ እቅድ በጋዜጠኛና የፖለቲካ አክትቪስት አበበ ገላዉ እንዲሁም በሌሎች ተቃዉሞ መሰረዙ አንዱ የሰሞኑ ክስተት እንደነበር አንድ ባልደረባችን ገለጸልን። እዚህ ላይ መረጃዉን በጊዜዉ አግኝተን ብንዘግብበት ተገቢ መሆኑን እንገልጻለን። ሆኖም በኢሳት ቴሊቪዥን እንደተነገረዉ፤ ኢሳት ከሁለት ሳምንታት በፊት ርእሱ ላይ መዘገቡን በማወቅ የኢሳትንም ሆነ የአቶ አበበ ገላዉን “ተአማኒነት ለማጥፋት”፤ የነሐሴ 6ቱን ፕሮግራም ባጠናቀረዉ ጋዜጠኛ ሄኖክ ሰማእግዜርም ሆነ በዋና አዘጋጅዋ ትዝታ በላቸዉ የተደረገ ደባ እንደሌለ ማስገንዘብ እንወዳለን።

በአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ አሰራርና ዘገባዎች ላይ ትችቶችና ቅሬታዎች ከተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ መንግስታትና ለውጥ አራማጆች ይሰማሉ። ከኢትዮጵያ መንግስት የአማርኛው ዝግጅት ክፍል ለተቃዋሚዎች “ያዳላል” የሚል ባለ 42 ገጽ ክስ ከሶስት ዓመት በፊት ቀርቦበታል። ቪኦኤም ገለልተኛ አጣሪ ቡድን በመመደብ በአግባቡ አጣርቶ ምላሽ ሰጥቶበታል። አቶ አበበ ገላውም በዝግጅታችን ላይ ቅሬታ ሲያቀርብ የመጀመሪያው አይደለም። ከዚህ ቀደም የቮኦኤን ዘገባዎችና ጋዜጠኛ ገለልተኝነት ከጥያቄ የሚያስገቡ ተቃውሞዎችን አቅርቧል። የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ በነዚህ ክስተቶች ላይ ተገቢውን ማጣራት አድርጎ፤ በዘገባዎቹና አሰራሩ የሚተማመን መሆኑን አሳውቋል። በዚህም መሠረት የዝግጅት ክፍላችን በማንኛውም ጊዜ የሚቀርቡ ቅሬታዎችንና ትችቶችን በአግባቡ ተቀብሎ፤ ተገቢውን ማጣሪያ የማድረግ፤ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ምላሽ ይሰጣል። የጋዜጠኝነት መርሆም ይሄው ነውና።

የሆነ ሆኖ ከክፍላችን ባልደረባ ያገኘነዉ አቶ አበበ ገላዉ ከአዙሳ ፓሲፊክ ዩኒቬርሲቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ Rachel White ጋር የተለዋወጠዉ የኢሜል መልክት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማክበር ተጀምሮ የነበረዉ ዝግጅት መሰረዙን ስለሚጠቁም፡-

1ኛ- በዳያስፓራዉና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ያለዉ ግንኙነት መሻከር ማሳያ በመሆኑ

2ኛ- አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ የአገሪቱ መሪ እንደመሆናቸዉ ዜናዉ አንድምታ ስላለዉ በመጨረሻዉ ደቂቃ በዝግጅቱ ለማካተት በጋራ ወሰንን።

ስነስርዓቱ የተሰረዘበትን ሁኔታ ከዩኒቨርሲቲዉ ማጣራት ዘገባችንን የተሟላ እንደሚያደርገዉ በማመን፤ ወደ ዩኒቬርሲቲዉ ቃል አቀባይ Rachel White ስልክ መደወል አስፈላጊ ነበር። ፕሮግራሙን ያቀናበረዉ ሔኖክ ይህን ለማጣራት ጊዜዉ ስላልነበረዉ ሌላ የክፍላችን ባልደረባ የዩኒቨርሲቲውን ሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ በማነጋገር መልሱን በጽሑፍ ተቀበለ። በነገራችን ላይ የRachel White ድምጽ “ለምን አልተቀዳም?” የሚል ጥርጣሬ የተሞላበት ተቃዉሞ ፕሮግራሙን ከሚተቹ ይሰነዘር ነበር። የተሰጠዉ ቃል በትክክል እስከ ተቀመጠ ድረስ አሰራሩ በጋዜጠኝነት ሙያ የተለመደ እንደሆነ ልናስገነዝብ እንወዳለን። በዚህ አሰራር መሰረት የተሰጠው ቃል በድምጽ ካልሆነ፤ በስልክ ወይንም በጽሁፍ የተሰጠውን ምላሽ አንቀበልም አንልም።

የሆነ ሆኖ Rachel White የዩኒቨርሲቲዉ ባለስልጣናት በዩናይትድ ስቴይትስ የውጭ ጉዳይ መስሪያቤት የተጻፈዉን የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ መብት አያያዝ በመገምገም ላይ እያሉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃለማሪያም ደሳለኝ ደዉለዉ መገኘት እንደማይችሉ በመናገራቸዉ ስነስርዓቱ መሰረዙን በቃል ገልጹልን። የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ገለልተኛ አጣሪ ቢሮ ፕሮግራሙ የተሰረዘበትን ምክንያት ለማወቅ ወደ Rachel White ባደረገዉ የስልክ ጥሪ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊዋ ይህንኑ ለአማርኛዉ አገልግሎት የሰጡትን ምክንያት ነዉ የደገሙት።

በዘገባችን የተጠቀሰዉ ምክንያት ግን “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰለ ሰረዙ” የሚለዉ ብቻ በመሆኑ፣ የዩኒቨርሲቲዉ ሹማምንት የኢትዮጵያን መንግስት ሰብአዊ መብት ይዞታ እየገመገሙ እንደነበር ባለመጥቀሳችን አድማጮቻችንን ይቅርታ እንጠይቃለን። በኢትዮጵያ ያለዉን የሰብአዊ መብት ሁኔታ በየጊዜዉ ስለምንዘግብና ወደፊትም መዘገባችንን ስለምንቀጥል ከዚህ ሪፓርት ዉስጥ ሆን ብለን የምናወጣበት ምክንያት አይኖርም።

እንደ ሌሎች ጋዜጠኞች ሁሉ ታዲያ እኛም ሰዎች በመሆናችን አንዳንዴ በሰዓቱ ፕሮግራም ለማድረስ ስንጣደፍ፤ ወይም በአንድ ርእስ ላይ ያለን መረጃ የተሟላ ሳይሆን ሲቀር ስህተት እንሰራለን። ሆኖም መስሪያ ቤታችን እነዚህን ስህተቶች ተቀብሎ የማረም ግልጽ ፖሊስ ይከተላል።

የአዙሳ ዩኒቨርስቲ ቃል አቀባይ የጠቅላይ ሚኒስትር ኋይለማርያም ደሳለኝ የክብር ስነስርዓት መሰረዝን አስመልክቶ የሚሰጡን አዲስ መረጃ ካለ ማብራሪያ እንዲሰጡ በስልክ ጋብዘናል።

Rachel White በመጀመሪያ በዉሳኔዎቻችን ሁሉ እግዚአብሔር ቀደሚ ነዉ ከሚለዉ ዋናዉ መርሆችንና እምነታችን በላይ የሆነ እንደሌለ በመግለጽ ልጀምር ካሉ በሁዋላ

“የዩኒቬርሲቲዉ አመራር አባላት በቅርቡ የአሜሪካ ዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የኢትዮጵያ ፌዴራል ከፈተኛ ፍርድ ቤት በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ላይ ያሳለፈዉን ዉሳኔ አስመልክቶ የወጣዉ መግለጫ ጭምር በኢትዮጽያ የሚካሄዱ ጉዳዮችን እየተከታተሉ ሳለ ወዲያዉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዟቸዉን በአጭር እንደሚቆርጡ መልዕክት ደረሰን። ስለዚህ ስነስርዓታችን ተሰረዘ።”

የትኛዉ ነጥብ ነዉ ለዩኒቨርሲቲዉ ባለስልጣናት ዉሳኔ ዋና መሰረት የሆነዉ? የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስነስርዓቱ ላይ እንደማይገኙ እናንተን ማሳወቅ ወይስ የሰብአዊ መብት ጉዳይ? ለሚለዉ ጥያቄያችን Rachel White መልስ ሲሰጡ: “ዩኒቨርሲቲዉ የሰብአዊ መብት መከበር በጣም ያሳስበዋል። እግዚአብሔርን እንደሚያስቀድም አንድ የክርስቲያን ተቋም። ሆኖም የክብር ስነስርዓቱ የተሰረዘበት ምክንያቶች ተከታታይ ናቸዉ። የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ አሳስቦን ዜናዎችን እየተከታተልን ሳለ፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰልክ ደዉለዉ ለክብር ስነስርዓቱ እንደማይገኙ ገለጹልን።”

የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ስነስርዓቱን እንድትሰርዙ ያደረጉት ጥረት የቱን ያህል ሚና ነበረዉ?

Rachel White ይመልሳሉ:- “እንዳልኩት ዩኒቨርሲቲዉ ለዉሳኔዎቹ ሁሉ መሰረት የሚያደርገዉ እግዚአብሔር ቀዳሚ ነዉ የሚለዉን መተክሉን ነዉ። ስለዚህ በዉጪ ድርጅቶች እኛን ማግባባት ሳይሆን የዉስጥ መርሃችን ላይ ነዉ ያተኮርነዉ።”

ቀድሞዉኑ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ የክብር ስነስርዓት ማድረግ ከየት ነዉ የመነጨዉ?”

“ስለዚያ ልናገር አልችልም። የዚያ ዉሳኔ አካል አልነበርኩም።” ነበር ያሉት Rachel White

አቶ አበበ ገላዉ ሰለ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ሽልማት መሰረዝ የቪኦኤ አማርኛ አገልግሎት የዩኒቨርሲቲውን ቃል አቀባይ ጠቅሶ ባቀረበው ዘገባ የተሰጠዉ ምክንያት ሰህተት መሆኑን በመጠቆም በተደጋጋሚ ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ሃላፊዎች ደብዳቤ ጽፏል። የበኩሉን እንዲያስረዳ ጠይቀናል።

(በአማርኛ የሰጠውን ቃል ከዚህ ዘገባ ጋር አያይዘናል)

አቶ አበበ ገላይ ከላይ ያቀረባቸውን ነጥቦች እናመሳክር፡

1ኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ “ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንዳለባቸው በመግለጻቸው” የሚለው የRachel White ቃል ነው። በኛ ዘገባ ከፊትም ከኋላም አልተባለም።

2ኛ ዝግጅቱ የተሰረዘው በአበበ ገላውና ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ መብት “ጫና” በሚል አቶ አበበ ያቀርበው መረጃ በእርግጥም በኛ ዘገባ “ጫና የሚል ቃል አልተጠቀምንም”

“በGARE እና በራሱ የቀረበ ተቃውሞ ውሳኔው መቀልበሱን በዘገባ አስፍሯል” ነው የሚለው። ይህንም ያገኘንው ረቡእ ጁላይ 23 በ1.07 PM ላይ ባሳተመው “ዩኒቨርስቲው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ክብር ገፈፈ” በሚል ርእስ ባሰፈረው ጽሁፍ ላይ ነው። እንዲህ ይላል “ የአሜሪካ ወንጌላዊት ዩኒቨርስቲው አስተዳደር ውሳኔውን ያሳለፈው ባለፈው ዓርብ በጠራዉ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ይሄ ዘጋቢ (አቶ አበበ ገላውን ማለቱ ነው) በርካታ የተቃውሞ ጥያቄዎችን በማንሳት፤ የሰብዓዊ መብት ለሚጥስ ሰው ክብር መስጠት ከAPU መመሪያ ቃል ጋር አብሮ ይሄዳል ወይ የሚል ጥያቄ ካነሳ በኋላ ነው።

3ኛውና የመጨረሻው ነጥብ “ደብዳቤ አልጻፍኩም” የሚለው ሲሆን፤ ይህንን የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ያገኘው አቶ አበበ ገላው ለባልደረባችን በላከው ኢ-ሜይል ነው። የተላከው የኢሜይል መልዕክት ከአሱዛ ፓሲፊክ ዩኒቨርስቲ ቃል አቀባይ ሬቸል ዋይት ጋር በጁላይ 17 እና 19 የተለዋወጠው ሲሆን፤ ቃሉንም የወሰድነው አቶ አበበ ገላው ከላከልን የኢሜይል ልዉውጥ ነው። በዘገባችን “ደብዳቤ” ነው ያልንው-- “ኤሌክትሮኒክ ደብዳቤ (ኢ-ሜይል)” በሚል እናርማለን።

የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ አስተዳደር አቶ አበበ ገላውና የዋሽንግተን ዲሲ ኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጣምራ ግብረ-ሃይል ያቀረቡትን ተቃውሞ በገለልተኛ አጣሪ ቡድኑ ወደ እንግሊዘኛ አስተርጉሞ ይዘቱን መገምገሙን ገልጾናል። መስሪያ ቤቱ የደረሰባቸዉን ግኝቶች ቀጥለን እናቀርባለን።

1ኛ፡ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የአማርኛዉ ቋንቋ አገልግሎት በዘገባዉ ለኢትዮጵያ መንግስት ወገንተኝነትን አላሳየም።

2ኛ፡ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ በዚያ ዘገባ ያቀረበዉ የአዙሳ ዩኒቬርሲቲዉ የክብር ስነስርዓት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሰረዙ ነዉ ማለቱ “ትክክል ነዉ”። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደዉለዉ ከመሰረዛቸዉ በፊት ዩኒቬርሲቲዉ የሰብአዊ መብት አያያዛቸዉን ይገመግም ነበር የሚለዉ የሕዝብ ግንኙነትዋ መልስ ባለመካተቱ ታሪኩን በስፋት ማስረዳት ይችሉ የነበሩ ጭብጦችን አስቀርቷል።

3ኛ፡ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የአማሪኛዉ ቋንቋ ዝግጅት ነሃሴ 6 ቀን ያስተላለፈዉ ፕሮግራም የኢትዮጵያን መንግስት የሚቃወሙ ወገኖችን አስተያየት በስፋት ያስተናገደ፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስትን የሚደግፉ ወገችን ሃሳብ በበቂ ያላካተተ ነዉ ብሏል።

የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ነሐሴ 6ቀን ያስተላለፈዉ ፕሮግራም ጋዜጠኞቹ ከእለት ተእለት ዜናዎች አልፈዉ በየጊዜዉ ጥልቀት ያላቸዉ ትንታኔዎችና አስተያዬቶችን ለፕሮግራሙ ተከታታዮች ለማቅረብ የሚያደርጉት ጥረት ምሳሌ ነዉ።

አብዛኞቹ ኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ለአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ጋዜጠኞች አስተያየታቸውን መስጠት ያለመፈለጋቸው፤ የተሟላና የሁሉንም ወገኖች አስተያየት የያዙ ዘገባዎችን ለማቅረብ ለምናደርገው ጥረት ፈታኝ ነው።

በሌል ጎን ደግሞ ተቋማዊና ሙያዊ ሚናችንን የሚገነዘቡ ያሉትን ያህል፤ የኢትዮጵያን መንግስት ከሚቃወሙ ወገኖች አሜሪካ ድምጽን የነርሱ ድምጽ አድርጎ የመውሰድ ግምት ይታያል።

በዩናይትድ ስቴይትስ ኮንግረስ በጀት የሚመደብለት አሜሪካ ድምጽ፤ ገለልተኛ፣ ነጻና የታመነ የዜና ምንጭ ነው። በጋዜጠኝነት ስራዎቹና በመዝናኛ ዝግጅቶቹ የአሜሪካን ባህል፣ የዴሞክራሲና የነጻነት መርሆዎችን ከወቅታዊ ዜናና ትንታኔዎች ጋር ከማቅረብ ባሻገር በቻርተሩ እንደተቀመጠው አሜሪካ ድምጽ “የዩናይትድ ስቴይትስ መንግስት ልሳን አይደለም”።

ይሄን ተቋማዊ ነጻነት አስፍተን ስንመለከተው ቪኦኤ የየትኛውም ሃገር መንግስት ሆነ ተቃዋሚ፣ ወይንም ለውጥ አራማጅ ቡድን፤ ደጋፊም ተቃዋሚም አይደለም። ቪኦኤ ነጻ ተቋም ነው።

የአሜሪካ ድምጽ ጋዜጠኞችም ስራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት፤ በመረጃ የተደገፉ ሃቆችን፣ ሚዛናዊ ዜናዎችና መረጃዎችን ከማንም ሳይወግኑ የተሟላ ማብራሪያ እንዲያቀርቡ የሚመሩበት የጋዜጠኝነት ሙያ ሰነድ ያዛል። የUnited States ምክር ቤት ባጸደቀዉ ደንብ ላይ የተዘተዘሩትን የጋዜጠኝነት መርዎች ተከትለን አሁንም ወደፊትም እንሰራለን።

በየቀኑ ስለምታዳምጡንና በምናቅርብላችሁ ፕሮግራሞቻችን ለምትሰጡን አመኔታ አድማጮቻችን እናመሰግናለን።

XS
SM
MD
LG