ኢራን የአሜሪካ ድምፅ የፋርስ ቋንቋ ጋዜጠኞችን ፀረ-መንግሥት ፕሮፓጋንዳ በማሰራጨት ወንጀል ከሳ፣ በሌሉበት ጥፋተኛ የሚል ውሳኔ ማሳለፏን የአሜሪካ ድምፅ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አወገዙ።
የጥፋተኝነት ውሳኔው ይፋ ይተደረገው፣ ባለፈው ሳምንት የኮምፒዩተር ጠላፊ ቡድን አባል የሆነው አዳላት አሊ የኢራንን የፍርድቤት ሰነዶችን ለሕዝብ ይፋ ባደረገበት ወቅት ሲሆን፣ መረጃዎቹ የታህራን አብዮታዊ ፍርድቤት፣ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 ዓ.ም በምስጢር ባካሄደው ችሎት፣ በደርዘን ለሚቆጠሩ የአሜሪካ ድምፅ ጋዜጠኞች እና ሌሎች የምዕራብ ዜና ማሰራጫዎች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዳሳለፈ ያሳያሉ።
የአሜሪካ ድምፅ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ጆን ሊፕማን ማክሰኞ እለት ባወጡት መግለጫ "እነዚህ የኢራን ድርጊቶች ለሰብአዊ መብት ወይም ለሕግ የበላይነት ዋጋ የማይሰጥ መንግሥት የሚያደርጋቸው ናቸው። በኢራን ነፃ የመረጃ ፍሰት እንዳይኖር ለማስቆም የሚደረጉ ጥቃቅን ሙከራዎችም ናቸው። የአሜሪካ ድምፅ የፋርስ ቋንቋ አገልግሎት የሴቶችን መብት፣ በነፃነት የመናገር እና በኢራን ውስጥ ነፃ ማህበረሰብ የመኖርን አስፈላጊነት በማሰራጨት ስኬታማ ሚና ያለው መሆኑንም የሚያሳዩ ናቸው። የአሜሪካ ድምፅ ከጋዜጠኞቹ እና ከዘገባዎቻቸው ጎን ይቆማል" ብለዋል።
በኒው ዮርክ የሚገኘው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢራን ልዑክ ቡድን በሊፕማን መግለጫ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ የአሜሪካ ድምፅ በኢሜይል ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
ከኢራን ፍርድ ቤት ሾልከው የወጡት እና ተዓማኒነታቸው በአሜሪካ ድምፅ ፋርስ ቋንቋ ክፍል የተረጋገጡት ሰነዶች፣ 11 የአሜሪካ ድምፅ ፋርስ ቋንቋ ጋዜጠኞችን እና የአገልግሎቱ የቀድሞ ዳይሬክተር የነበሩትን ሴታራህ ደራክሼህ ሲግን፣ በመንግሥት ላይ ፕሮፓጋንዳ በማሰራጨት ብያኔ እንደተላለፈባቸው ያሳያሉ።
ሰነዶቹ በስም የተገለጹት ግለሰቦች ያልተገለጸ የእስር ቅጣት እንደተፈረደባቸው እና ውሳኔው ተፈፃሚ እንዲሆን ለኢራን አቃቤ ሕግ ቢሮ፣ የሚዲያ እና ባህል ጉዳዮች መላኩንም ያመለክታል። ሊፕማን በመግለጫቸው "የአሜሪካ ድምፅ ስማቸው የተጠቀሱት ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸው የተሻለ ጥበቃ የሚያገኙበትን መንገድ እየገመገመ ነው" ያሉ ሲሆን ያንን ለማድረግ በውጪ ካሉ ኤጀንሲዎች እና ከሚመለከታቸው ጋራ አብረው እንደሚሠሩ አመልክተዋል።
የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባቸው 11ዱ የአሜሪካ ድምፅ የፋርስ ቋንቋ አራት ሴት ጋዜጠኞች፡ ኻሚድ አራሚድ፣ ሳራ ደህጋኻን፣ ፋህሜህ ከዝር ሄይዳሪ እና ማህታብ ቫሂዲ ራድ ሲሆኑ፣ ስድስቱ ወንድ ጋዜጠኞች ደግሞ፡ ማህዲ ፋላኻቲ፣ አርያን ሪስባፍ፣ አራሽ ሲጋርቺ እና ፓያም ያዝዲያን ናቸው።
ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የቋንቋው አገልግሎት ማኔጂንግ ኤዲተር ሲጋርቺ "እኛ እዚህ ወንጀል እየሠራን አይደለም። ህግ የምናከብር መልካም ዜጎች ነን። የኢራን ባለሥልጣናት የፖለቲካ መለያ እየለጠፉብን ነው። ነገር ግን በእስላማዊ ሪፐብሊክ ሕግም ቢሆን፣ የጋዜጠኝነት ሥራችን ወንጀል አይደልም" በማለት በፍርድቤቱ ውሳኔ ማዘኑን ገልጿል።
ሲጋርቺ አገሩን ጥሎ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከመምጣቱ በፊት፣ መንግሥት እውቅና በሰጠው የኢራን ጋዜጣ ላይ በዋና አዘጋጅነት በሚሠራበት ወቅት ሦስት ዓመት በኢራን እስርቤት አሳልፏል። አሁን የተላለፈበት ውሳኔም በአሜሪካ ድምፅ የፋርስ አገልግሎት በሚሠራው ሥራ ላይ ተጽእኖ እንደማያሳድርበት ገልጿል።
"ለኔ የመጀመሪያ ጊዜዬ አይደለም። እንደ ጋዜጠኛ ዜና ስንሠራ ፍትሃዊ እና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ነው። ስለዚህ በኛ ላይ ተፅእኖ አይኖረውም። ምክንያቱም እኛ ሥራችንን ነው የምንሠራው።"
ከአሜሪካ ድምፅ ጋዜጠኞች በተጨማሪ ሌሎች 30 በምዕራብ ሀገራት የውጪ ሚዲያ ላይ የሚሠሩ ጋዜጠኞች በፕሮፓጋንዳ ወንጀል ተከሰው እንደተፈረደባቸው ተጠልፎ የተገኘው ሰነድ ያመለክታል። ከነዚህ ውስጥ የአሜሪካ ድምፅ እህት ጣቢያ የሆነው ራዲዮ ፋርዳ፣ የቢቢሲ የፋርስ ቋንቋ አገልግሎት፣ ኢራን ኢንተርናሽናል እና ማኖቶ የተሰኙት ጣቢያዎች ይገኙበታል።
መድረክ / ፎረም