በኦሮሚያ ክልል፣ በሴቶች የሚመራ የሲቪል ድርጅቶች ጥምረት በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም፣ በተለይ በክልሉ ግጭት በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች አስቸኳይ ርምጃ እንዲወሰድ ጠየቀ። በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱት የሴቶች ሰላም ግንባታ ትስስር አዲስ አበባ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ባለሥልጣናት እና ባለድርሻ አካላት እየተባባሰ ያለውን ችግር እንዲፈቱ አሳስበዋል።
አዶዬ የኢትዮጵያ ሴቶች ብቃት ማዕከል የተሰኘ ተቋም ዋና ሥራ አስፈፃሚ፣ ወይዘሮ ደራርቱ መርጋ በመግለጫው ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች በአሳሳቢ ደረጃ መጨመሩን አመልክተው፣ አፋጣኝ ጣልቃ ገብነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በግጭት ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ተመጣጣኝ ያልሆነ ስቃይ አጉልተው ያስረዱት የፍራቴሎ ገባሬ ሰናይ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳርቱ ሸምሰዲን በበኩላቸው፣ በፕሪቶሪያ በተፈረመው የሰላም ስምምነትም ኾነ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል እና በክልሉ ማዕከላዊ አካባቢዎች የቀድሞ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አዛዥ የነበሩት ሰኚ ነጋሳ መካከል በተደረገው ስምምነት ውስጥ ምንም ዐይነት የሴቶች ተሳትፎ አለመኖር እጅግ አሳሳቢ መሆኑን አመልክተዋል።
የአሜሪካ ድምፅ በተነሱት ሐሳቦች ዙሪያ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትን እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ለማናገር ቢሞክርም ምላሽ አልሰጡም። ይሁን እንጂ ሁለቱም ወገኖች ከዚህ ቀደም በሰጧቸው መግለጫዎች፣ ሴቶች እና ሕፃናትን ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ያደርሳሉ በሚል የሚቀርብባቸውን ክስ ውድቅ አድርገዋል።
ዘገባው የገልሞ ዳዊት ነው።
መድረክ / ፎረም