ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በ75 ዓመታቸው ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ከቆዩ አንጋፋ የፖለቲካ ሰዎች መካከል አንዱ መሆናቸው የሚነገርላቸው በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር)÷ የተፎካካሪ ፓርቲው የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ነበሩ፡፡ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ሕልፈተ-ሕይወት የተሰማውን ሐዘን ገልፆ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ዕንቁ ምሁራን መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱ፣ ተመራማራ፣ መምህር፣ በሳል ፖለቲከኛና ብቁ አመራር ነበሩ ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በየነ ጴጥሮስ ህልፈት አስመልክቶ በአስተላለፉት የሐዘን መግለጫ መልዕክት፣ “ያቆዩት ውርስ እና ቅርስ ፀንቶ እንዲቀጥል ነፍሳቸውም በሰላም እንድታርፍ እመኛለሁ” ብለዋል፡፡
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሙያ፤ በመንግሥታዊ የሥራ መዋቅር ውስጥም በትምህርት ሚኒስትር ዴኤታነት እንዲሁም የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በመሆን ህይወታቸው እስካለፈበት ቀን አገልግለዋል።
በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሹመው ሲያገለግሉ ነበር፡፡
መድረክ / ፎረም