በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቫቲካን ጾታ መቀየርን፣ የማኅፀን ኪራይ እና ውሰትን ተቃወመች


በቫቲካን የአቡነ ፍራንሲስ የቅርብ አማካሪ የሆኑት የአርጀንቲናው ካርዲናል ቪክቶር ማኑኤል ፈርናንዴዝ በቫቲካን በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት እአአ ሚያዝያ 8/2024
በቫቲካን የአቡነ ፍራንሲስ የቅርብ አማካሪ የሆኑት የአርጀንቲናው ካርዲናል ቪክቶር ማኑኤል ፈርናንዴዝ በቫቲካን በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት እአአ ሚያዝያ 8/2024

ጾታን ለመቀየር የሚደረግ ቀዶ ጥገና እና አንዲት ሴት በሰው ሰራሽ መንገድ ለሌሎች ጸንሳ እና አርግዛ የምትወልድበት የማኅፀን ኪራይ እና ውሰትን ፣"በሰው ልጅ ክብር ላይ የተጋረጡ አደጋዎች ናቸው"ስትል ቫቲካን ዛሬ ተቃውሞዋን አሰምታለች።

የሮማ ካቶሊክ ቤት ክርስቲያን ዋና መቀመጫ የሆነችው ቫቲካን ዛሬ ይፋ ባደረገችው 20 ገፅ ሰነድ ፣ ጾታን ለመቀየር የሚደረግ ቀዶ ጥገና እንዲሁም አንዲት ሴት ለሌሎች ጸንሳ እና አርግዛ የምትወልድበት መንገድ ከጽንስ ማቋረጥ እና የታካሚን ስቃይ ለማስቆም በሕክምና የሚፈጸም ሕይወት ማጥፋት ጋራ የሚመሳሰል እንደኾነ ገልፃለች። እነዚህ ድርጊቶች "እግዚያብሔር ለሰው ልጅ ሕይወት ካለው ዕቅድ ጋራ የሚጻረሩ ናቸው" ብላለች ቤተክርስቲያኗ ባወጣችው በዚኹ መግለጫ።

“ወሰን የሌለው ክብር” በሚል ቤተክርስቲያኒቱ ባወጣችውና ለአምስት ዓመታት ሲሰናዳ የቆየ ነው በተባለው ሰነድ፣ የአንድን ሰው ጾታ መቀየር ይቻላል የሚለውን ሃሳብ በድጋሚ ተቃውማለች፡፡

እግዚያብሔር ሴትና ወንድ ብሎ ለይቶ በመፍጠሩ፣ ይህን ለመቀየር መሞከሩ፣ ከጽንሰት ጀምሮ የሰው ልጅ የተሰጠውን ልዩ ክብር የሚጻረር እንደሆነ ቫቲካን አስታውቃለች፡፡

ባለፈው ወር በሮማው ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የተፈረመው ሰነድ፣ ጾታ መቀየርን በመለከተ ጠንካራ ተቃውሞ ቢሰነዝርም፣ የተመሳሳይ የጾታ ግኙነትን በተመለከተ ግን ለየት ያለ አቋም የያዘ ይመስላል። “የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ወንጀል አይደለም” የሚለውን የአቡነ ፍራንሲስን አቋም በመከተል፣ በተለይም በአፍሪካ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ፈጻሚዎች ላይ የሚደርሰውን እስር እና ስቃይ ሰንዱ ተቃውሟል።

በቫቲካን የአቡነ ፍራንሲስ የቅርብ አማካሪ የሆኑት የአርጀንቲናው ካርዲናል ቪክቶር ማኑኤል ፈርናንዴዝ የተመሳሳይ ጾታ ትዳር ፈፃሚዎችን መባረክ የሚፈቅድ ሰነድ በቅርቡ ማውጣታቸው በመላው ዓለም፣ በተለይም በአፍሪካ የሚገኙ ወግ አጥባቂ ሊቀ ጳጳሳት ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞን አስነስቷል።

በሰው ልጅ ክብር ላይ አደጋ የደቀኑት ድህነት፣ ጦርነት፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ለስደት መዳረግ ናቸው የሚለውን የሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ አቋም ሰነዱ እንዳንጸባረቀም የአሶሽየትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG