የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝደንት ጄ ዲ ቫንስ በፓሪስ በመካሄድ ላይ ባለው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ጉባኤ ላይ በመገኘት ሥልጣን ከያዙ ወዲህ የመጀመሪያ የኾነውን የውጪ ጉዞ አድርገዋል።
በጉባኤው ከበድ ያሉ ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች እንደሚደረጉ ሲጠበቅ፣ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማትም በፍጥነት በማደግ ላይ ባለው የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ውስጥ የበላይነትን ለመያዝ ጥረት ያደርጋሉ ተብሏል።
በሁለት ቀናቱ ጉባኤ ላይ ከ100 የሚሆኑ ሀገራት የተውጣጡ የመንግሥታት መሪዎች፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች እና የሳይንስ ሰዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
ጉባኤው ለበርካታ የአውሮፓ መሪዎች ጄ ዲ ቫንስን ለመጀመሪያ ጊዜ ለማገኘት አጋጣሚውን ይፈጥርላቸዋል ተብሏል።
“ከዚህ በፊት ብዙም ባልታየ የቴክኖሎጂ እና የሳይንስ አብዮት በሚካሄድበት ወቅት እንገኛለን” ብለዋል ከ ጄ ዲ ቫንስ ጋራ የምሳ ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ የሚጠበቁት የፈረንሣዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን። የዩክሬን እና የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች በአጀንዳ ከተያዙት ውስጥ እንደሚገኝበት የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።
እንደ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ሁሉ፣ ምክትል ፕሬዝደንት ጄ ዲ ቫንስም አሜሪካ ለዩክሬን በምትሰጠው የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንን በሚያገለው አካሄድ ላይ ጥያቄ አላቸው።
መድረክ / ፎረም