አዲስ አበባ —
ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ እንደምትሰጥ ይፋ ካደረገችው የዘጠና ሰባት ሚሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ በተጨማሪ ሊለዋወጡ ለሚችሉ ሁኔታዎች ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን አንድ የዓለምአቀፍ የልማት ኤጀንሲዋ - ዩኤስኤአይዲ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የበረታ ረሃብ ወይም ቸነፈር ይከሰታል ብለው እንደማያስቡ ግን ኃላፊዋ አመልክተዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የአጣዳፊ ጊዜ ድጋፍ በቀጥታ ለመንግሥት የሚሰጥ ሳይሆን በአጋሮቻቸው አማካይነት የሚደርስ መሆኑን የኤጀንሲው የምሥራቅ፣ የመካከለኛውና የደቡባዊ አፍሪካ ክፍል ኃላፊ ሬቸል ግራንት ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሠረት በካቶሊክ የተራድዖ ድርጅት አማካይነት የ58 ሚሊየን ዶላር ግምት ያለው የአሜሪካ ምግብ እንደሚቀርብና በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል ደግሞ ለረሃብ መከላከያ 19 ሚሊየን ዶላር እንዲሁም ለስደተኞች ድጋፍ 20 ሚሊየን ዶላር የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል፡፡
ግንራትን በስልክ ያነጋገራቸው እስክንድር ፍሬው ያጠናቀረውን ዘገባ የያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡