የዩናይትስ ስቴትስ የዓለም አቀፍ የልማት ኤጄንሲ (ዩኤስኤአይዲ) ብሔራዊ የኤድስ መረጃና የምክር አገልግሎት ማዕከልን ለኢትዮጵያ መንግሥት አስረክቧል።
ባለፉት 12 አመታት ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ ውስጥ ከኤድስ ጋር በተያያዘ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ መርዳቷ ተጠቁሟል። ከኤችአይቪ/ኤድስ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ብቻ ይውሉ የነበሩ የማዕከሉ አገልግሎቶች ለሌሎች ብሔራዊ የጤና ጉዳዮችም ክፍት እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የዩናይትስ ስቴትስ የዓለም አቀፍ ልማት ኤጄንሲ ከጆንስ ሆፕኪስን ዩኒቨርሲቲ የተግባቦት መርኃ ግብሮች ማዕከል ጋር በመሆን የኤጄንሲውን የጤና ተግባቦት አቅም ግንባታ የጋራ ፕሮጀክት ቁልፍ የተባሉ የአገልግሎት ዘዴዎችን ዛሬ ረፋድ ላይ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተካሄደ ሥነ-ሥርዓት ለሚኒስቴሩ አስረክቧል፡፡
ይህ በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ሲመራ የቆየ ፕሮጀክት የያዛቸው ቁልፍ የአገልግሎት መስጫ ዘዴዎች ብሔራዊ ወገን የቀጥታ ጥሪ ማዕከልን፤ በኤድስ ዙሪያ የተለያዩ ግብአቶችን የሚያቀርብ ቤተ-መፃህፍትን፤ በርካታ አድማጮች ያላቸውን ኤችይቪን በመከላከል ላይ የሚያተኩሩ የራድዮ ፕሮግራሞች እና በጤና ጥበቃ በኩል በማኅበራዊ የጠባይና የአኗኗር ለውጥ ዙሪያ የሚሠጡ ሥልጠናዎችን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች የተካተቱትበት ነው።
ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡