በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሁለት ለጋሽ አካላት የትግራይ ርዳታ ሥርጭታቸውን በጊዜያዊነት አቋረጡ


ሁለት ለጋሽ አካላት የትግራይ ርዳታ ሥርጭታቸውን በጊዜያዊነት አቋረጡ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:31 0:00

ሁለት ለጋሽ አካላት የትግራይ ርዳታ ሥርጭታቸውን በጊዜያዊነት አቋረጡ

የዩናይትድ ስቴትስ የዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ/USAID/ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም/WFP/፣ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የሚያከናውኑትን የምግብ ርዳታ ሥርጭት በጊዜያዊነት ማቋረጣቸውን አስታውቀዋል፡፡ ለጋሽ ድርጅቶቹ፣ ከዚኽ ውሳኔ ላይ የደረሱት፣ ለርዳታ የገባው እህል ለገበያ በመቅረቡ ነው፤ ብለዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ጉዳዩን የሚያጣራ ግብረ ኃይል ማቋቋሙን አስታውቋል። ሰብአዊ ርዳታ እንዲከፋፈል ማመቻቸት እንጂ የርዳታ እህል ማከፋፈል ሥራው አለመኾኑን የገለጸው የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ፣ የሚደረገውን ምርመራ እንደግፋለን፤ ብሏል።

የዩናይትድ ስቴትስ የዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ፣ ወደ ትግራይ ክልል የሚላከው የርዳታ እህል በጊዜያዊነት መቋረጡን ያስታወቀው፣ ትላንት ረቡዕ፣ ሚያዝያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በአወጣው መግለጫ ነበር። የርዳታ ሥርጭቱን በጊዜያዊነት የማቋረጥ ውሳኔ ላይ የደረሰው፣ ከምርመራ በኋላ እንደኾነም ገልጿል፡፡

የልማት ኤጀንሲው አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር፣ ውሳኔው ከባድ እንደኾነ በአመለከቱበት በዚኽ መግለጫ፣ ረኀብ መሰል ጥኑ ችግር ውስጥ ለሚገኙ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ለማዳረስ ታልሞ የተላከው የምግብ ርዳታ፣ ወደ ሌላ አቅጣጫ ተቀይሶ ለአካባቢው ገበያ በመሸጥ ላይ ስለ መኾኑ ኤጀንሲው እንደደረሰበት አስታውቀዋል።

የሽያጭ ድርጊቱን፣ ወደ ዋና መሥሪያ ቤቱ የምርመራ ክፍል አቅርቦ የማጣራት ሥራ መጀመሩን አስተዳዳሪዋ ገልጸዋል፡፡ የምግብ ርዳታ ሥርጭቱን በጊዜያዊነት ለማቆም ከመወሰኑም በፊት፣ ከኤጀንሲው ቢሮ የተውጣጡ አመራሮችን ለማጣራት ሒደቱ ወደ ኢትዮጵያ መላኩን ፓወር አውስተዋል፡፡

የተደረገውን ምርመራ ተከተሎም ኤጀንሲው፣ ዐዲስ አበባ ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እና ከሌሎች አጋሮች ጋራ በመቀናጀት፣ የምግብ ርዳታን በጊዜያዊነት ማቆም ከሁሉ የተሻለው ርምጃ እንደኾነ ከውሳኔ ላይ መድረሱን ገልጿል።

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት፣ ስጋቱን፣ ለኢትዮጵያ ፊዴራል መንግሥት እና ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሥልጣናት ማሳወቁን የገለጹት ፓወር፣ ባለሥልጣናቱም፣ የድርጊቱን ፈጻሚዎች በመለየት ተጠያቂ ለማድረግ ፈቃደኝነታቸውን መግለጻቸውን አመልክተዋል፡፡

ጠንካራ የቁጥጥር ርምጃ ሲወሰድ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፥ የዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ የርዳታ መርሐ ግብሯን እንደምትቀጥል የተናገሩት ፓወር፣ ርዳታችን ለታቀደላቸው የችግር ተጋላጭ ማኅበረሰቦች እንደሚደርስም መተማመን እንችላለን፤ ብለዋል፡፡

ርዳታው ከታለመለት መዳረሻው ወጥቶ መገኘቱ፣ በሁለት ዓመቱ ጦርነት ሳቢያ ለከፍተኛ የምግብ ዋስትና ዕጦት ለተዳረጉ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ንጹሐን ሰላማዊ ሰዎች፣ ሌላ ተጨማሪ ጉዳት መኾኑን የልማት ኤጀንሲው አስታውቋል።

የኤጀንሲው አስተዳዳሪ ፓወር አያይዘውም፣ “በትግራይ ክልል የሚሠራጨው የምግብ ርዳታ በጊዜያዊነት ቢቋረጥም፣ ተጨማሪ ሕይወት አድን የተመጣጠኑ ምግቦችን፣ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ፣ እንዲሁም የግብርና እና የልማት ድጋፍን የመሳሰሉት ወሳኝ ርዳታዎች ይቀጥላሉ፤” ብለዋል፡፡

ጦርነቱን ለማቆም በፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ፣ ተጨማሪ የርዳታ አቅርቦት ወደ ክልሉ እንዲገባና ተቋርጠው ከነበሩ አገልግሎቶች አንዳንዶቹ እንዲቀጠሉ አስችሏል፡፡

ዩኤስኤአይዲ፣ ለአሜሪካ ግብር ከፋዮች ተጠያቂ እንደኾነ ሓላፊነት የሚሰማው ተቋም፣ ጠንካራ የቁጥጥር፣ የክትትል እና የግምገማ ሥርዓቶችን በመተግበር፣ ሰብአዊ የርዳታ እህል ለታለመላቸው ችግረኞች ብቻ እንዲውሉ ያደርጋል፤ ብሏል።

የርዳታው በጊዜያዊነት መቋረጥ፣ አስቀድሞም በእጥረት ላይ ላሉት ሲቪሎች፣ ተጨማሪ ጉዳት የሚያስከትል መኾኑን ያመለከቱት ሳማንታ ፓወር፣ ዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመርዳት ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ

ይህን የለጋሾች ጊዜያዊ ውሳኔ በተመለከተ፣ በዛሬው ሳምንታዊ መግለጫቸው ላይ የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም፤ ርዳታ እንዲከፋፈል ማመቻቸው እንጂ ርዳታ ማከፋፈል የመንግሥት ሥራ አለመኾኑን ገልጸው፣ መንግሥት በለጋሽ ድርጅቶች በኩል የሚደረገውን ምርመራ እንደሚደግፍ ተናግረዋል፡፡

“ለሰብአዊ ድጋፍ የመጣ ርዳታ ለሰብአዊ አገልግሎት መዋል አለበት፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ ልምድ ብቻ ሳይሆን አሠራርም ነው፤” ያሉት መለስ ዓለም፣ “ከዚኽ አንጻር የኢትዮጵያ መንግሥትን ሚና በውል ማወቅ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ “የኢትዮጵያ መንግሥት ርዳታ አያከፋፍልም፡፡ ርዳታ ለሚያከፋፍሉ አካላት ኹኔታዎችን ነው የሚያመቻቸው፡፡ ጸጥታውን ያስጠብቃል፤ ቦታውን ያመቻቻል፤ ርዳታ የማከፋፈል ሥራው፣ ርዳታውን የሚሰጡ አካላት ነው፤” ብለዋል።

ቃል አቀባዩ አያይዘውም፣ የሚካደው ምርመራ ተገቢ ነው፤ ርዳታለተረጂው እንዲውል ማድረግ ያስፈልጋል፤ ወገኖቻችን ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ ሚደረገው ጥረትገባሬ ሠናይ አካላት ጋመንግሥት ተባብሮ ይሠራል፤ ይነጋገራል ብለዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራምም እንዲኹ፣ የርዳታ ሥርጭቱን ማቋረጡን ገልጿል፡፡

በተመሳሳይ ዜና፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል፣ ሰብአዊ የምግብ ርዳታ ከታቀደው ውጭ መዋላቸውን የሚያሳዩ የቅርብ ጊዜ ዘገባዎች፣ በእጅጉ እንዳሳሰቡት፣ ትላንት በአወጣው መግለጫ አስታውቋል። “ተቋማችን፣ ጉዳዩን በጥብቅ የሚይዘው ከመኾኑ በተጨማሪ፣ አስፈላጊ የምግብ ድጋፎችን፣ ለችግር ተጋላጭ ለኾኑ ሴቶች፣ ወንዶች እና ሕፃናት በማዳረስ ሒደት ውስጥ የሚፈጠር ጣልቃ ገብነትን አይታገሥም፤” ብሏል።

“የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ዘገባውን ከተመለከተ በኋላ በአስቸኳይ ጥልቅ ምርመራ ጀምሯል። ሐቁን ለማወቅና ቁጥጥሩን ለማጠናከር አፋጣኝ ርምጃዎችን ወስዷል። በትግራይ ክልል ውስጥ ሲያደርግ የቆየውን የምግብ ርዳታ ሥርጭት ያቋረጠ ሲኾን፣ በእጅጉ አስፈላጊ የኾኑ ርዳታዎች፣ ለታለመላቸው ተረጂዎች መድረሳቸውን እስካላረጋጋጠ ድረስ፣ ሥርጭቱን ድጋሚ አይጀምርም፤” ሲል አስታውቋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም፥ በዚኽ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ውስጥ የተሳተፉትን ለመለየት፣ ተረጂዎችን በመለየትና በመመዝገብ ሒደት ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን ለመድፈን፣ ከክልሉ ባለሥልጣናት ጋራ በቅርበት እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ተቋሙ፥ የሥራ አጋሮቹ፣ ሕገ ወጥ ተግባራትን እንዲቆጣጠሩና እንዲያሳውቁ፣ ስምምነት የተደረሰባቸውን የቁጥጥር መንገዶች እንዲያስፈጽሙ፣ በድጋሚ ጥሪ አቅርቧል፡፡ አያይዞም፣ “የክልሉን ሕዝብ 84 በመቶ ነዋሪ ለምግብ ቀውስ ከዳረገውና ሁለት ዓመትን ከፈጀው ግጭት ገና እያገገመ ነው፤” ያለው የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ሕይወት አድን ድጋፎች በእጅጉ ለሚያስፈልጓቸው ሰዎች በብቃት እንዲዳረሱ ለማድረግ በጽኑ ቁርጠኛ እንደኾነ አስታውቋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምላሽ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ላለፉት ጥቂት ሳምንታት፣ በጉዳዩ ላይ፥ ከዲፕሎማቶች፣ ከዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች ተወካዮች እና ከክልሉ የማኅበረሰብ ተወካዮች ጋራ መወያየታቸውን ጠቅሰው፣ ጉዳዩን አጣርቶ ሕጋዊ ርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ግብረ ኃይል እንዲቋቋም መወሰኑን፣ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

አቶ ጌታቸው በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ደብዳቤ፣ በጦርነት እና በመፈናቀል የከፋ ችግር ውስጥ ወድቆ ሰብአዊ ርዳታ በመጠባበቅ ላይ ያለውን ሕዝብ ለማዳን የተለገሰው እህል ለሽያጭ መቅረቡ፣ ከሕዝቡ እና ከተራድኦ ድርጅቶቹ ከፍተኛ ቅሬታ እየቀረበበት ስለመኾኑ ተጠቅሷል።

“ይህ ተግባር ደግሞ፣ በረኀብ አለንጋ እየተገረፉ በሚገኙ ሕፃናት፣ አረጋውያን፣ የአካል ጉዳተኞች እና በሕመም በሚሠቃዩ ወገኖች ላይ የሚፈጸም ተጨማሪ በደልም ወንጀልም ነው፤” ያለው ደብዳቤው፣ እንደ ሕዝብም እንደ መንግሥትም ሊታገሡት የማይገባ በመኾኑ፣ አድራጎቱ እንዳይደገም ከመከላከል ጀምሮ ቀደም ሲል የተፈጸሙ ጥፋቶችን አጣርቶ፣ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የሚያስችል ክልላዊ ግብረ ኃይል ማቋቋም አስፈላጊ ኾኖ መገኘቱን አስረድቷል፡፡ ክልላዊ ግብረ ኃይሉን በመምራት ውሳኔውን እንዲያስፈጽሙ፣ ሌፍተናንት ጀነራል ፍሥሓ ኪዳኑ መመደባቸውንም አስታውቋል፡፡

የተቋቋመው ግብረ ኃይል፣ ከክልል እስከ ጣቢያ ኮሚቴዎችን በማደራጀት፣ ወንጀል የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂነት እንዲያረጋግጥ በጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንቱ ትእዛዝ ተሰጥቶታል፡፡ ሕዝብ፣ የጸጥታ እና የሕግ አካላት ከግብረ ኃይሉ ጋራ በመተባበር እንደሚሠሩ እምነታቸውን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ ዕንቅፋት ለመፍጠር የሚሞክሩ ግለሰቦችም ኾኑ የመንግሥት አካላት ከድርጊታቸው በአፋጣኝ እንዲቆጠቡ በጥብቅ አሳስበዋል፡፡ ግብረ ኃይሉ፣ የደረሰበትን ውጤት እና የሥራውን አፈጻጸም አስመልክቶ፣ ለሕዝብ እና ለሚመለከታቸው አካላት ይፋዊ መግለጫ እንደሚሰጥም በደብዳቤው ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም፣ “ለችግሩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በአጭር ጊዜ እንደሚፈታ፣ ለለጋሽ ሀገራት በተለይም ደግሞ ለዓለም የምግብ ፕሮግራም ለማረጋገጥ እወዳለኹ፤” ያሉት የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንቱ፣ ረጂ ድርጅቶቹ የሰብአዊ ርዳታውን ሥርጭት ለማቋረጥ በቅርቡ ያስተላለፉት ውሳኔ፣ ወትሮም በችግር ላይ ያለውን ሕዝብ የባሰ የሚጎዳው በመኾኑ፣ በድጋሚ እንዲያጤኑትና የተለመደውን የድጋፍ ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

በፌዴራሉ መንግሥት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል፣ ለሁለት ዓመታት በተካሔደው ጦርነት፣ በመቶ ሺሕዎች የተቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ ሚሊዮኖችን ለከባድ ረኀብ ዳርጓል፤ ብዙ ሚሊዮኖችም ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡

XS
SM
MD
LG