በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሳማንታ ፓወር ምሥራቅ አፍሪካ ናቸው


የዩናይትድ ስቴትስ የዓለምአቀፍ ልማት ኤጀንሲ /ዩኤስኤአይዲ/ ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር
የዩናይትድ ስቴትስ የዓለምአቀፍ ልማት ኤጀንሲ /ዩኤስኤአይዲ/ ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር

በምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች ውስጥ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የዩናይትድ ስቴትስ የዓለምአቀፍ ልማት ኤጀንሲ /ዩኤስኤአይዲ/ ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ለድርቅና ለረሃብ ከተጋለጡ ኬኒያዊያን ጋር ተወያተዋል።

አካባቢው ላይ የደረሰውን ድርቅና የምግብ ቀውስ አጉልቶ ለማሳየት የታለመ ነው በተባለ ጉብኝታቸው ሚስ ፓወር የኬኒያ ቱርካና ክፍለ ግዛት ካቾዳ መንደር ነዋሪዎችን ሄደው አነገግረው ድርቁ በማኅበረሰቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ሰፊ ጉዳትና የደቀነውን የቸነፈር ሥጋት ተመልክተዋል።

"ያነጋግርኳቸው እናቶች ልጆቻቸው በአጣዳፊ የተመጣጠነ ምግብ ዕጥረት ተጎድተውባቸዋል። እንስሶቻቸው በሙሉ አልቀውባቸዋል። በመተዳደሪያቸው ላይ ብርቱ ጉዳት ደርሷል፤ ሰዎች በገፍ ለሞት የሚጋለጡበት አደጋም ተደቅኗል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

“ዩናይትድ ስቴትስ ለአጋሮቿ የአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ትለግሳለች” ብለዋል ሳማንታ ፓወር።

ለአራት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ሳይጥል በቀረበት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የከፋ ሰብዓዊ አደጋ መደቀኑን የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት፣ የእርዳታ ድርጅቶችና ሌሎችም ለበርካታ ወራት ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።

ባለፈው ዓርብ የምሥራቅ አፍሪካ ሃገሮች የጋራ ልማት ተቋሙ ኢጋድ ያወጣው ግምገማ በክልሉ ዙሪያ በዚህ የአውሮፓ ዓመት ከሃምሳ ሚሊዮን የሚበልጥ ሰው ለአጣዳፊ የምግብ እጥረት እንደሚጋለጥ አሳስቧል።

በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን ሦስት መቶ ሺህ ሰዎች ለአጣዳፊ የረሃብ ቸነፈር እንደሚጋለጡ ኢጋድ ሥጋቱን አክሎ አሳውቋል።

XS
SM
MD
LG